
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የባሕል ፍርድ ቤቶች እውቅና መስጫ እና የሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር አካሄዷል።
በመርሐ ግብሩ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ የፌደራል እና የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ከየወረዳው የተወከሉ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው መርሐ ግብሩ የባሕል ፍርድ ቤቶች ሥራቸውን እንዲጀምሩ የሚያግዝ መኾኑን ገልጸዋል።
ግጭት እና አለመግባባት ተፈጥሯዊ ክስተት ነው፤ ዋናው ጉዳይ ግን ችግሮችን ከመሰረቱ መፍታት እና ግንኙነትን በዘላቂነት ጠግኖ ሰላምን ማስፈን መቻል ነው ብለዋል። በርካታ ሀገራት በባሕላዊ ዘዴ የሚዳኙበት ሰፊ አማራጭ እንዳላቸው ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያም አለመግባባቶችን የምታርቅባቸው የጎለበቱ ሀገር በቀል ባሕላዊ ዘዴዎች ያሏት ሀገር ናት ብለዋል።
ይህ የሀገሪቱ የዳበረ እና ጠቃሚ ባሕል በበቂ ሁኔታ የሕግ ጥበቃ ሳይደረግለት እና በሕግ እውቅና ሳይሰጠው ለረጅም ጊዜ መቆየቱንም ገልጸዋል።
ዜጎች በባሕላዊ ፍርድ ቤቶች የመዳኘት፣ ባሕላቸውን የመጠቀም እና የማስፋፋት መብት እንዳላቸው የገለጹት ፕሬዝዳንቱ መንግሥትም የመደገፍ ኀላፊነት የተሰጠው ቢኾንም ዝርዝር ሕግ ወጥቶ ወደ ተግባር ሳይገባ ቆይቷል ነው ያሉት።
በ2016 ዓ.ም ግን ሀገር አቀፍ የዳኝነት እና የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ትግበራ መጀመሩን ተከትሎ በአማራ ክልልም አለመግባባቶችን ለመፍታት ያለውን የቆየ እና የዳበረ ባሕል መሰረት በማድረግ እና በጥናት በመለየት ወደ ተግባራዊ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል።
ለባሕል ፍርድ ቤቶች እውቅና መሰጠቱ የሽማግሌዎች ውሳኔ አስገዳጅ እና የሕግ እውቅና ያለው እንዲኾን፣ የሕዝብም እውቅና እና ድጋፍ እንዲሰጠው፣ ማኅበረሰቡም በአንድነት እና በሰላም የመኖር ባሕሉን እንዲያጎለብት የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የባሕል ፍርድ ቤቶች ዳኝነትን የሚሰጡ በመኾናቸው ተጠሪነታቸውም ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መኾኑን ገልጸዋል። የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሚናም መደገፍ እና አቅማቸውን መገንባት ነው ብለዋል።
በዚህም መሰረት እውቅና ተሰጥቷቸው ሥራ የጀመሩት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች 15 አይነት ናቸው። ሽምግልና፣ አበጋር፣ ረከቦት፣ ዱለት፣ አማሬ ቁና፣ አውሳይድ፣ ጎራው አባ አሊ፣ ስምንቱ ማይ ቤት፣ ዘወልድ፣ መዛርድ፣ ክፍሎ፣ ሰንዬሰገድ፣ አባ ሀጋ፣ ዙፋን ዋልዋጅ እና ሰባቱ ከዘራ ናቸው ብለዋል።
እነዚህ የባሕል ፍርድ ቤቶች ተደራሽ እና ወጭ ቆጣቢ ናቸው፤ ክርክሮችን በአሸናፊ እና ተሸናፊነት ሳይኾን በእርቅ የሚፈቱም መኾናቸውን ገልጸዋል። ማኅበረሰቡ በሰላም፣ በአንድነት እና በመከባበር እንዲኖርም ከፍ ያለ ጠቀሜታ እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
በማቋቋሚያ አዋጁም የገንዘብ ክርክርን ጨምሮ የተለያዩ ጉዳዮችን እንዲያዩ ሥልጣን መሰጠቱን አንስተዋል። አነስተኛ የወንጀል ጉዳዮችንም እንደሚዳኙ ገልጸዋል። እርቅ ማውረድ እና ካሳ መወሰንም ይችላሉ ብለዋል።
ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ሁለቱም ተከራካሪዎች ወደው እና ፈቅደው በባሕላችን እንዳኛለን ብለው የሚሄዱባቸው አማራጭ ሥርዓቶች ናቸው፤ ፍርድ ቤትን ግን ሊተኩ እንደማይችሉ ገልጸዋል። የሚሠሩትም ዘመናዊ ሕግን ጠቅሰው ሳይኾን ባሕላዊ እሴቶችን ታሳቢ አድርገው ነው ብለዋል።
እውቅና የተሰጣቸው ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች በክልሉ ከ4 ሺህ በላይ ቀበሌዎችን ተደራሽ አድርገው እንደሚሠሩም ተናግረዋል። የባሕል እሴቶችን በአግባቡ ጠብቆ ለመያዝ እና ነጻ ኾነው እንዲሠሩ የሚያስችል ሥልጠና እና የተግባቦት ስትራቴጂም መዘጋጀቱን አመላክተዋል።
መንግሥት እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት ባሕላዊ ፍርድ ቤቶችን እንዲደግፉም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
