በፕላን የተመሩ የገጠር ማዕከላት እንዲገነቡ ማድረግ ይገባል።

11
አዲስ አበባ፡ ታኅሣሥ 21/2018ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የገጠር ማዕከላት ልማት የንቅናቄ መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።
“በፕላን የተሠሩ የገጠር ማዕከላት ለዘላቂ የከተማ ልማት፤ በአንድ ወረዳ አንድ የገጠር ማዕከል ዕውን ይኾናል” በሚል መሪ መልዕክት በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ባለው ሀገር አቀፍ የንቅናቄ መድረክ የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ተገኝተዋል።
ሚኒስትሯ የመጠለያ ቤቶች ታሪካዊ እና ባሕላዊ ጥበብን የምናንጸባርቅባቸው የማንነት መገለጫ ናቸው ብለዋል። መጠለያ ቤቶች ለአብዛኛው ሕዝብ የኑሮ ዋስትና ማረጋገጫ ቅርስ እንደኾኑም ጠቁመዋል።
ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳቸውም የጎላ ነው ብለዋል። መንግሥት ለከተሞች ትኩረት በመስጠት የቤቶችን ፖሊሲ እና ስትራቴጂ በመቅረጽ ውጤታማ ሥራዎች እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በከተሞች የቤት አቅርቦትን በተለያዩ አማራጮች እና በተመጣጣኝ ዋጋ ዜጎች የሚያገኙበት ሁኔታ እየተፈጠረ እንደኾነም አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት የዜጎችን የቤት ፍላጎት ለማሟላት በርካታ ሥራዎች የተሠሩ ቢኾንም የቤት አቅርቦትን ለመመለስ ብዙ ይቀራል ነው ያሉት።
አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል በገጠር የሚኖር እንደመኾኑ መጠን ደረጃቸውን ያልጠበቁ ቤቶች ያሉበት እና መሠረተ ልማቶች ያልተሟሉሏቸው ናቸው ብለዋል።
የተሟላ ብልጽግናን ማረጋገጥ የሚቻለው የገጠር ማዕከላትን በፕላን በመሥራት በመሠረተ ልማት ማስተሳሰር ሲቻል እንደኾነም አብራርተዋል።
የገጠር ማዕከላት ነገ ከተማ እንደሚኾኑ በመገንዘብ ደረጃቸውን የጠበቁ ቤቶች እና በፕላን የተመሩ የገጠር ማዕከላት እንዲገነቡ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የከተማ እና ገጠር ትስስርን ለመፍጠር በመሠረተ ልማቶች ማስተሳሰር እና ተደራሽ ማድረግ ቀዳሚ አጀንዳ መኾኑንም ገልጸዋል።
መድረኩ ዘርፉ ላይ ላሉ ሰዎች የአቅም ግንባታ ሥራ የሚሠራበት፣ የልምድ ልውውጥ የሚካሄድበት እንዲኾን ለማድረግ ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት።
ሁሉም ክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ሥራውን በትኩረት መሥራት እንዳለባቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዘጋቢ፦ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ቂምና ጥላቻ የሚያሽርባቸው፣ ወዳጅነትም የሚጸናባቸው ናቸው ” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next article“ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ሁለቱም ተከራካሪዎች ወደው እና ፈቅደው የሚሄዱባቸው አማራጭ ሥርዓቶች ናቸው” አቶ ዓለምአንተ አግደው