
ባሕር ዳር: ታሕሣሥ 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የባሕል ፍርድ ቤቶች እውቅና መስጫ እና የሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር አካሄዷል። በመድረኩ ላይ ተገኝተው የሥራ መመሪያና መልእክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች አለመግባባቶችን ለመፍታት የምንጠቀምባቸው አኩሪ ባሕሎች መኾናቸውን ጠቅሰዋል። እነዚህ ባሕሎች የማኅበራዊ መስተጋብር የደም ስሮች ናቸውም ብለዋል።
የአማራ ክልል መንግሥትም ይህንን በመረዳት ለነዚህ ባሕሎች እውቅና በመስጠት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በአዋጅ ጭምር መደንገጉን ተናግረዋል። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ 15 ባሕላዊ የግልግል እና የሽምግልና ሥርዓቶች ዕውቅና የተሰጣቸው ሲኾን ሌሎች ያልተደረሰባቸው ባሕላዊ ሥርዓቶች ሊኖሩ እንደሚችሉም ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል።
ባሕላዊ ሥርዓቶች ለዘመናት የኖሩ፤ ሕዝቡ የዕለት ከዕለት አለመግባባቶችን የሚፈታባቸው፣ ቂምና ጥላቻን የሚያሽርባቸው፣ ወዳጅነትንም የሚያጸናባቸው ሰለመኾኑም ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል። መደበኛው የፍትሕ ሥርዓት ተደራሽ ሳይኾን ቢቀር ሊፈጠር የሚችለውን ክፍተት በመሙላት በኩልም የጎላ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
የማሕበረሰቡ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶችን እንደ አማራጭ የመጠቀም ልምድ ከፍ ያለ ስለመኾኑ የጠቀሱት ርእሰ መሥተዳድሩ “ሰማይ ቢቀደድ በሽማግሌ ይሰፋል” የሚለው አባባል የዚህ ማሳያ ስለመኾኑ አንስተዋል። ውስብስብ ችግሮች ቢገጥሙ እንኳን የሀገር ሽማግሌዎች በዳበረ ክሕሎት፣ ልምድ እና ጥበብ መፍትሔ ያበጁለታል፤ ሕዝባችንም በባሕላዊ የእርቅ ሥርዓቶች ላይ የጸና እምነት አለው ብለዋል።
ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው ቢኾንም ይህ ነው የማይባል የሕግ ድጋፍ ሳይደረግላቸው መቆየታቸውን ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል። ይህም ከጊዜ ወደጊዜ እንዲዳከሙ እና ጉዳዮች ሁሉ ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት እንዲያመሩ እና ፍርድ ቤቶችም እንዲጨናነቁ አድርጓል ነው ያሉት።
የፍትሕ አገልግሎቱ ውጤታማነት ከፍ ያለ እንዲኾን መደበኛው ፍርድ ቤት እና ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ጎን ለጎን መሥራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል። ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች መደበኛው ፍርድ ቤት ከሚሰጣቸው ብያኔዎች በላይ የማኅበረሰቡን መልካም መስተጋብር እንደሚያረጋግጡም ጠቁመዋል። ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ማኅበራዊ ፍትሕን ለማንገሥ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸውም ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል።
ባሕላዊ ፍርድ ቤቶችን ለማጠናከር የክልሉ መንግሥት አሥፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል። ከቤተሰብ እስከ ማኅበረሰብ ድረስ የሚገጥሙ ግጭቶች እንዲፈቱ እና ሰላም እንዲነግሥ በሚያስችል መልኩ ሥራቸውን እንዲያከናውኑም መልእክት አስተላልፈዋል።
ለባሕላዊ ፍርድ ቤቶች እውቅና መስጠት ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት የሰዎችን ፍትሕ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት ለማስፋት እና ተደራሽ ለማድረግ በማሰብ ነው። ባሕላዊ ሥርዓቶቹ ኅብረተሰቡን የሚመስሉ እና በቀላሉ ተደራሽ በመኾናቸው የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋግጣሉ፤ የመንግሥትን እና የሕዝብን ግንኙነትም ከፍ ያደርጋሉ ነው ያሉት።
ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች እንዲያድጉ እና እንዲጎለብቱ አላግባብ ከኾኑ ጣልቃ ገብነቶች መቆጠብ እንደሚገባም ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል።
በአሠራርና ጥበባቸው ላይ ተጽእኖ ማሳደር አይገባም ነው ያሉት። ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች የበለጠ እንዲዳብሩ እና ሕዝብን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ሁሉም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
