
ባሕርዳር፡ ታኅሣሥ 21/2018ዓ.ም (አሚኮ) በሀገር መከለካያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች እዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ በብላቴ ልዩ ዘመቻዎች እዝ ማሠልጠኛ ማዕከል በመገኘት ከመሪዎች እና ከሠልጣኞች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም ሀገራችን ከፋታዋን ለማረጋገጥ በምታደርገው ሁለንተናዊ ግስጋሴ የመከላከያ ሠራዊት እና የጸጥታ ኀይሎች በፅናት መቆማቸውን ገልጸዋል።
የሕዝብን አንድነት ለማናጋት ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር አስበው በሚንቀሳቀሱት ላይ ሠራዊቱ አሥፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ ፍላጎታቸውን ትርጉም ወደሌለው ደረጃ ማድረሱንም ተናግረዋል።
ታጣቂዎች የቀረበውን የሠላም ጥሪ እየተቀበሉ ነው ያሉት አዛዡ በመልካም አቀባበል ወደ ኅብረተሰቡ ተቀላቅለው የሠላም አጋዥ መኾን የሚችሉበት ሁኔታ እየተመቻቸ መኾኑን ገልጸዋል።
የልዩ ዘመቻዎች እዝ ወርቃማ ታሪካዊ ጀግንነት እየፈጸመ መምጣቱን አንስተዋል። አሁንም ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ፣ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅም እንዲረጋገጥ የኮማንዶ፣ የአየር ወለድ፣ የልዩ ኀይል እና ጸረ ሽብር ክፍሎች ግዳጃቸውን በታማኝነት በቁርጠኝነት በታታሪነት እየተወጡ መኾኑን ገልጸዋል።
ከሀገር መከለካያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ሠልጣኞችም ይህንን ወርቃማ ታሪክ ለማስቀጠል ሥልጠናቸውን በአኩሪ ውጤት ማጠናቀቅ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የልዩ ዘመቻዎች እዝ ምክትል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ከማል ኢቢሶ የልዩ ዘመቻዎች እዝ ብዙ ወርቃማ የጀግንነት ታሪክ ያለው ክፋል መኾኑን ገልጸዋል። ይህንኑ ታሪክ የተረከቡ የጽናት እና ንጋት ኮርስ ሠልጣኞች ሥልጠናቸውን በተነሳሽነት፣ በሀገር ፍቅር ስሜት እና ሙያዊ ክብር በመውሰድ ሀገር ተረካቢነታቸውን በተግባር ማረጋገጥ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
