“የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራ ሰው እና ተፈጥሮን ያስታርቃል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

5
ደሴ: ታኅሣሥ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የ2018 ዓ.ም የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት በደቡብ ወሎ ዞን በአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ ተጀምሯል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራ ለግብርና ሥራዎች መሠረት መኾኑን አመላክተዋል።
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራዎች በምርት እና ምርታማነት ላይ ውጤት መታየቱን ገልጸዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት የአካባቢን ሥነ ምህዳር መሠረት ያደረጉ የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ሥራዎች በመከናወናቸው የተፈጥሮ ሚዛንን መጠበቅ እንደተቻለ አመላክተዋል።
በተሠሩ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሦራዎች እርጥበት አጠር በነበሩ አካባቢዎች ምንጮች ጎልብተዋል ነው ያሉት።
የተራቆተን አካባቢ ተንከባክቦ ከተፈጥሮ ጋር ማስታረቅ ያስፈልጋል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ተፈጥሮ እና ሰው ተስማምቶ የሚኖርበት ሀገር እንዲኖረን እንፈልጋለን፣ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራ ሰው እና ተፈጥሮን ያስታርቃል ብለዋል።
በለሙ ተፋሰሶች ወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እየኾኑ መኾናቸውንም ገልጸዋል። በማሳያነት በአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ ደልመኔ ተፋሰስ ላይ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የኾኑ ወጣቶችን አንስተዋል።
የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራ የአካባቢን ሥነ ምህዳር በመጠበቅ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ተሳታፊ የሚኾንበት ሥራ እንደሚከናወንም ገልጸዋል።
ከዛሬ ታኅሣሥ 20/2018 ዓ.ም ጀምሮ 456 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ እንደሚከናወንም አመላክተዋል።
ክልሉን ወደተሟላ ሰላም ለማሸጋገር ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
“በዚህ ዘመን ከደም አፋሳሽ ግጭት ተላቀን ላባችንን በማፍሰስ ኑሯችንን ለማሸነፍ በትጋት ልንሠራ ይገባል” ነው ያሉት።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የክልል እና የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ:- ጀማል ይማም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሚሊሻ ሁለገብ የሰላም እና የልማት አርበኛ ነው።