
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው የባሕል ፍርድ ቤቶች እውቅና መስጠትን እና ወደ ሥራ ማስገባትን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የባሕል ፍርድ ቤቶች እውነትን በማውጣት ፍርድን ለመስጠት አይነተኛ የፍትሕ መንገዶች ናቸው ብለዋል።
ሽምግልናን መሠረት አድርገው የሚሠሩ በመኾናቸው እርቅን በማምጣት፣ የበደለን እንዲክስ በማድረግ፣ ቁርሾን በማስቀረት ዘላቂ እና ጤናማ የማኅበረሰብ ግንኙነትን ለመፍጠር አይነተኛ ሚና አላቸው ነው ያሉት። በመንግሥት በኩልም ዜጎች ባሕላቸውን እንዲያሳድጉ እና በመረጡት የመዳኘት መብታቸው እንዲከበር ኀላፊነት ያለበት በመኾኑ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት መኾኑን አንስተዋል።
በክልሉ ምክር ቤት የባሕል ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም እና ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችል አዋጅ ወጥቶ ወደ ተግባር ተገብቷል ነው ያሉት። የአዋጁን አፈጻጸም የሚከታተል በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰብሳቢነት የሚመራ የአማካሪ ምክር ቤት መቋቋሙንም ጠቁመዋል። እስከ ቀበሌ ድረስ ጥናቶችን ማድረግ፣ የእውቅና መስጫ እና የማስተግበሪያ መመሪያ ማውጣት፣ የትግበራ ፍኖተ ካርታ እና የሥልጠና ሰነዶችን ማዘጋጀት፣ የተግባቦት ስትራቴጅ መቅረጽ እና ሌሎች ሰፊ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውንም አንስተዋል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም አዋጁን በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር እና የባሕል ፍርድ ቤቶችን ሥራ ለማስጀመር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጸዋል። ታኅሣሥ 21 እና 22/2018 ዓ.ም በክልል ደረጃ የእውቅና እና የሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር እንደሚኖርም አስታውቀዋል። መርሐ ግብሩ ከየወረዳው የተወከሉ ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አዋጁን ለማሥፈጸም ኀላፊነት የተሰጣቸው ተቋማት፣ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት እንደሚከናወንም አብራርተዋል።
በክልሉ ከ4 ሺህ በላይ በኾኑ ቀበሌዎች ሥራው እንደሚጀመርም ገልጸዋል። በባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ተግባራዊ የሚደረጉ ሽምግልናን ጨምሮ 15 የባሕላዊ ግጭት መፍቻ ሥርዓቶች መለየታቸውንም ተናግረዋል። በቀጣይም ጥናት እየተደረገ ሊጨመር እንደሚችል ጠቁመዋል።
“የባሕል ፍርድ ቤቶች የመደበኛ ፍርድ ቤቱን የሚተኩ ሳይኾኑ ጎን ለጎን የሚሠሩ የዜጎች አማራጭ የፍትሕ ሥርዓቶች ናቸው” ብለዋል። እውቅና ሲሰጣቸውም ባሕሉ እንዲዳብር ታሳቢ የተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል። ለዚህም የሚሰጧቸው ውሳኔዎች በአስገዳጅነት ተፈጻሚ እንዲኾኑ ተደርጓል ነው ያሉት።
ሥራቸውን ሲሠሩም የማኅበረሰቡን የባሕል እሴት በጠበቀ መልኩ የሚያከናውኑ ይኾናል ብለዋል። የባሕል ፍርድ ቤት ዳኛ ኾነው የሚመረጡ ሽማግሌዎች ገለልተኛ እና ታማኝ ኾነው ሰብዓዊ መብቶችን እና ሕገ መንግሥቱን የማክበር ኀላፊነት እንዳለባቸውም አብራርተዋል።ለባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ውጤታማነት እና ለአዋጁ ተግባራዊነት የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
