“በክልሉ የሚገኙ ፕሮጀክቶች የክልሉን ኢኮኖሚ ለማሳለጥ ሚናቸው ከፍ ያለ ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

6
ባሕርዳር፡ ታኅሣሥ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የመሠረተ ልማት ዘርፍ የ2018 በጀት ዓመት የአምስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) በአማራ ክልል በፌደራል እና በክልሉ መንግሥት እየተሠሩ የሚገኙ የመንገድ፣ የውኃ፣ የመስኖ፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማሰራጫ እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች፣ የደረቅ ወደብ፣ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ እና ሌሎች ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።
በእነዚህ ፕሮጀክቶች ላይ በፌደራል መንግሥት በኩል በድምር 185 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የሚገመቱ ፕሮጀክቶች በአማራ ክልል ውስጥ እየተሠሩ ነው ብለዋል። የክልሉ መንግሥት ደግሞ በየዓመቱ ከሚመድበው የካፒታል በጀት ከ50 እስከ 60 በመቶ የሚደርሰውን ለእነዚህ ዘርፎች እየመደበ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቶች የተለያየ አፈጻጸም አላቸው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳደሩ ግማሾቹ በጸጥታ ችግር ምክንያት የተቋረጡ እና የተጓተቱ ናቸው ብለዋል። ከፊሎቹ ደግሞ ሲገነቡ የፍጥነት ችግር ያለባቸው መኾናቸውን አንስተዋል። በማሳያነትም በአማራ ክልል እየተገነቡ ካሉ 61 የመንገድ ፕሮጀክቶች 12 የሚኾኑት በጸጥታ ችግር የተቆረጡ ናቸው ነው ያሉት።
በክልሉ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ለክልሉ ኢኮኖሚ አሳላጭ እና አቀላጣፊነት ያላቸው ሚና ከፍ ያለ ነው ብለዋል። ለነገ ኢኮኖሚ እድገት እና ብልጽግና አስቻይ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ በመኾኑ የፕሮጀክት ሥራዎችን ትኩረት ሰጥቶ መሥራት፣ መወያየት እና መገምገም ያስፈልጋል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየእስቴ – ስማዳ የአስፋልት መንገድ ግንባታ በታኅሣሥ 2018ዓ.ም መጨረሻ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው።
Next article“የባሕል ፍርድ ቤቶችን ሥራ ለማስጀመር ዝግጅቱ ተጠናቅቋል” አቶ ዓለምአንተ አግደው