
ደሴ: ታኅሣሥ 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የ2018 በጀት ዓመት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ማስጀመሪያ የንቅናቄ መድረክ በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከሚሴ ከተማ ከፍተኛ የክልል የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በክልሉ ባለፋት ዓመታት በተሠሩ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ተግባራት ምርት እና ምርታማነት እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል።
በተለይ ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በተተከሉ ችግኞች የአፈር መሸርሸርን ቀንሷል ነው ያሉት። የደን ሽፋንም እንደጨመረ ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት ከታኅሣሥ 20/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ከ20 እስከ 30 ቀናት ድረስ የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ይከናወናል ብለዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ደረጀ ማንደፍሮ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ የግብርና ተግባራት ሁሉ መሠረት መኾኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት በተሠሩ ተግባራት ምንጮች በመጎልበታቸውም የመስኖ ልማት ላይ ለውጦች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።
ወጣቶች በለሙ ተፋሰሶች ላይ የሥራ ዕድል እየተፈጠረላቸው መኾኑንም አንስተዋል።
“እንደ ክልል በዚህ ዓመት በ456 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 9 ሺህ 206 ተፋሰሶች ይለማሉ ነው” ያሉት።
ዘጋቢ:-ሰይድ አብዱ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
