
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ፖሊዮ ለበርካታ ዓመታት ሕጻናት ላይ የአካል ጉዳት እና የሥነ ልቦና ጫና እያደረሰ የቆዬ አደገኛ በሽታ ነው። ይህን በሽታ ለመከላከል በየጊዜው ለሕጻናት በዘመቻ መልክ ክትባት ይሰጣል።
የክትባቱን አስፈላጊነት ባለማወቅ፣ በቸልታ ወይም የፖሊዮ በሽታን አደገኝነት ባለመገንዘብ ሕጻናትን ተከታትሎ ለማስከተብ ጉትጎታዎች ሲደረጉ እናስተውላለን።
በባሕር ዳር ፈለገ ሕይዎት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕጻናት ስፔሻሊስት ዶክተር አያል መኳንንት ፖሊዮ በዐይን በማይታይ እና ፖሊዮ በተባለ ቫይረስ ምክንያት የሚመጣ ተላላፊ በሽታ ነው ብለዋል።
በሽታው ካልታከመ የማይመለስ የልጅነት ልምሻን እንደሚያስከትልም ነው የገለጹት። ትኩሳት፣ ራስምታት፣ ማስመለስ፣ ድካም፣ የእጅ እና የእግር ጡንቻ መድከም የበሽታው ዋና ዋና ምልክቶች መኾናቸውንም ተናግረዋል።
በሽታው በተበከለ ምግብ እና መጠጥ አማካኝነት፣ ከመጸዳጃ ቤት መልስ እጅን በተገቢው መንገድ ባለመታጠብ፣ የተበከለ ውኃ በመጠጣት እና ከተበከለ ውኃ ጋር የተገናኙ ምግቦችን በመጠቀም ይተላለፋል ነው ያሉት።
በተጨማሪም በተበከለ ውኃ ውስጥ በመዋኘት፣ ፖሊዮ ካለበት ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ በማድረግ እና በማስነጠስ ወይም በማሳል ጊዜ ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍ አንስተዋል።
ፖሊዮን እንዴት መከላከል ይቻላል? ብለን ለጠየቅናቸው ጥያቄም የፖሊዮ በሽታን መከላከል የሚቻለው በክትባት ብቻ ነው ብለውናል።
ማኅበረሰቡም ይህን በመገንዘብ ልጆቹን የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በሚካሄድበት ወቅት ሁሉም በትኩረት እንዲያስከትብ መክረዋል።
የፖሊዮ ክትባት በነጻ የሚሰጥ የሕጻናትን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስን አስፈላጊ ክትባት መኾኑንም ጨምረዋል።
ዘጋቢ:- ሰምሀል ፍስሐ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
