
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 16/2018 ዓ.ም አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
በጉባኤው ላይ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የአምስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
ሪፖርቱን ያቀረቡት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን ወርቅነህ እንዳሉት የሀገራችንን ቀጣይ ዕጣ ፋንታ ከሚወስኑ ጉዳዮች ውስጥ ትምህርት ዋነኛው መኾኑን በመገንዘብ ዘርፉን ከገጠሙት ፈተናዎች ለማውጣት በቅንጅት እየተሠራ ነው።
የትምህርት ጥራት እና ሽፋንን ለማሻሻል አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራ ቢኾንም አንጻራዊ መሻሻል እንጅ በሚፈለገው ደረጃ ግን ማሳደግ አልተቻለም ነው ያሉት።
ተፈላጊውን ውጤት ለማምጣት በልዩ ትኩረት እና በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅም አመላክተዋል። የ2018 የትምህርት ዘመን ከቅድመ አንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ድረስ በአጠቃላይ 7 ሚሊዮን 445 ሺህ 545 ተማሪዎችን ለመመዝገብ የታቀደ ቢኾንም የተመዘገቡት 4 ሚሊዮን 306 ሺህ 273 ተማሪዎች ናቸው ብለዋል።
ይህ የምዝገባ አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ሲነጻጸር የተሻለ ዕድገት ቢኖረውም ሥራው ግን ገና ሰፊ ርብርብ እንደሚፈልግ አብራርተዋል።
የተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ያለመምጣት ችግር ከዞኖች አኳያ ሲታይ በተለይም በጎጃም ዞኖች የሕጻናት ከትምህርት ገበታ የመነጠል የከፋ ችግር ስለመግጠሙ ቢሮ ኀላፊው ጠቁመዋል።
የትምህርት ቤት ምገባ ሥርዓት ለትምህርት ውጤት መሻሻል ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መኾኑን የጠቀሱት ቢሮ ኀላፊው በ2018 ዓ.ም ለምገባ መርሐ ግብር በአጠቃላይ 940 ሚሊዮን 421 ሺህ 125 ብር ተመድቧል።
እስካሁን ድረስም በ65 ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ 1ሺህ 107 ትምህርት ቤቶች ተደራሽ ኾነው 255 ሺህ 367 ተማሪዎች ተጠቃሚ ኾነዋል ነው ያሉት።
ከመጽሐፍት ሕትመት ጋር በተያያዘ በቀረበ ሪፖርትም ለሁለተኛ ደረጃ 11 ሚሊዮን 92 ሺህ 517 መጽሐፍት በትምህርት ሚኒስቴር ታትመው መሰራጨታቸው ተጠቅሷል። ከ11ኛ እና 12ኛ ክፍል የአፍ መፍቻ ቋንቋ ውጭ ባሉ የትምህርት አይነቶች የተማሪ መጽሐፍ ጥምርታ 1ለ1 ኾኗል ነው ያሉት።
ከትምህርት የራቁ ተማሪዎችን ለመመለስ እና የተመዘገቡትም በአግባቡ እንዲማሩ ለማድረግ በየአካባቢው የሚገኙ የምክር ቤት አባላት የሕዝብ እንደራሴነታቸውን በአግባቡ በመወጣት ዘርፉን እንዲደግፉም የትምህርት ቢሮ ኀላፊው ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
