
አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 90ኛ ዓመት የኢትዮጵያ አየር ኀይል የምሥረታ ቀን በአየር ኀይል ትርዒት፣ በአቭየሽን ቴክኖሎጅ ኤክስፖ፣ በአየር ኀይሎች ፎረም እና በሕዝባዊ ውይይት እንደሚከበር ተገልጿል።
የበዓሉን አከባበር አስመልክቶም ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት በኢፌዴሪ አየር ኀይል የአንደኛ አየር ምድብ አዛዥ እና የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ ሠብሣቢ ብርጋዴር ጄኔራል ብሩክ ሰይፉ የአየር ኀይሉ የምሥረታ በዓል ሕዝባዊነትን ማዕከል ባደረጉ የተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል ብለዋል።
ክብረ በዓሉ “የኢትዮጵያ አየር ኀይል የነፃነት እና የአንድነት ምልክት” በሚል መሪ መልዕክት ከጥር 15/2018 ዓ.ም እስከ ጥር 19/2018 ዓ.ም ድርስ በተለያዩ መርሐ ግብሮች መከበሩ እንደሚቀጥል በመግለጫቸው ገልጸዋል፡፡
በበዓሉ ከጥር 15/2018 ዓ.ም እስከ ጥር 19/2018 ዓ.ም በአይነቱ ለየት ያለ “የአንበሶች ሰማይ ኢትዮጵያ” በሚል መሪ መልዕክት የኢትዮጵያ አየር ኀይል፣ የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ የአየር ኀይል፣ የራሽያ የአየር ኀይል፣ የሞሮኮ የአየር ኀይል እና የቼክ ሪፐብሊክ የአየር ኀይል በጋራ የጥቁር አንበሳ የአየር ትርዒት እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
“የወደፊቱን የአቭዬሽን አቅም በጋራ እንገንባ” በሚል መሪ መልዕክትም የኢትዮጵያ አየር ኀይል፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የቻይና፣ የሕንድ፣ የአሜሪካ እና የደቡብ አፍሪካ ታላላቅ ኩባንያዎች፣ ከ25 በላይ የሚኾኑ በአቭዬሽን ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገራት የአቭየሽን እና የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት “ስታቲክ ዲስፕለይ” እና “የአቭዬሽን ቴክኖሎጂ ኤክስፖ 2026” እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡
በኢፌዴሪ አየር ኀይል 90ኛ ዓመት የምሥረታ ቀን በዓል ከ38 በላይ የአፍሪካ ሀገራት የአየር ኀይል አዛዦች የሚሳተፉበት እና “የጋራ ሥራዎቻችንን አጠናክረን የተረጋጋ ዓለም እንገንባ” በሚል መሪ መልዕክት በኢትዮጵያ አየር ኀይል አዘጋጅነት ፊውቸር አፍሪካ አየር ኀይሎች ፎረም ታላላቅ የአቭዬሽን ባለሙያዎች በተገኙበት እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ከአቭየሽን ቴክኖሎጂ ጋር ያላትን ቅርብ ትስስር በተግባር የሚያረጋግጥ እንደሚኾንም ተናግረዋል፡፡ ሌላኛው የምሥረታ ቀን በዓል መርሐ ግብር አካል የኾነው የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ የጦር አዛዦች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች “ሀገርን በማገልገል የሚገኝን ክብር መዘከር” በሚል መሪ መልዕክት ከኅብረተሰቡ ጋር በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ሕዝባዊ ውይይት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
የበዓል አከባበሩ አንዱ አካል የኾነ etaf90years.com የተሰኘ የኢቨንት ድኅረ ገጽ ይፋ መደረጉን ገልጸዋል። ድረ ገጹ የዝግጅቱን ዝርዝር የሚያሳይ እና የባለፉት ዓመታትን የተቋሙን የለውጥ ሂደት የሚያስቃኝ ነው ብለዋል።
በዚሁ ድኅረ ገጽ ሁሉንም የበዓሉ ኩነቶች ማግኘት፣ የመግቢያ ቲኬት መግዛት እና በድኅረ ገጹ ኩነቶቹን መከታተል እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡ እነዚህ የበዓል ሁነቶች ለሕዝቡ ክፍት መኾናቸውንም ተናግረዋል።
ጀግናው የኢትዮጵያ አየር ኀይል 90 ዓመታትን ባስቆጠረው የምሥረታ ታሪኩ የሀገርን ሉዓላዊነት በመጠበቅ አኩሪ ታሪክ ያለው ስመ ገናና ተቋም ነው፡፡
አየር ኀይሉ የኢትዮጵያን የአየር ክልል በጀግንነት ከመጠበቅ ባሻገር በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በመሰማራት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ አውለብልቧል። የሰላም አምባሳደርነቱንም በተግባር አሳይቷል፡፡
በሥልጠናው ዘርፍም ከራሱ አልፎ የሌሎች ሀገራት የአየር ኀይል ሙያተኞችን እያሠለጠነ ይገኛል፡፡
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም ሙሐመድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
