በኤርትራ መንግሥት በቀይ ባሕር አፋር ሕዝቦች ላይ እየደረሰ ያለውን ስልታዊ የዘር ማጥፋት ወንጀል ለማስቆም አህጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ተቋማት ጫና እንዲያሳድሩ የቀይ ባሕር አፋሮች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ጥሪ አቀረበ።

18
አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የቀይ ባሕር አፋሮች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት አጠቃላይ በቀይ ባሕር የአፋር ሕዝቦች ላይ በኤርትራ መንግሥት እየደረሰ ያለውን ግፍ እና ጭቆና አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
ድርጅቱ በደናክል አካባቢ በቀይ ባሕር አፋር ሕዝቦች ላይ እየተፈጸመ ያለው መጠነሰፊ፣ ስልታዊ እና መንግሥት መር የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተባባሰ መምጣቱን ነው በመግለጫው ያስታወቀው።
በመኾኑም ሕዝቡን ከሚደርስበት ችግር ለማዳን የሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ የአፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ የተመድ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማት ሕጋዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካዊ እርምጃ እንዲወስዱ አሳስቧል።
በቀይ ባሕር አፋር ሕዝቦች ላይ ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ እየደረሰ ያለውን መንግሥት መር የዘር ማጥፋት ግፍ በተመለከተ በመረጃ የተደገፈ አቤቱታ እና ክስ በጋምቢያ ለሚገኘው የአፍሪካ የሰብዓዊ እና የሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን ማቅረቡንም ድርጅቱ ገልጿል።
በኤርትራ ባለው አገዛዝ እየተፈፀሙ ካሉ የመብት ጥሰቶች መካከል ያለፍርድ ማሰር፣ መሰወር፣ ፆታዊ ጥቃት፣ ማንነት እና ባሕልን ማጥፋት፣ በግዳጅ ማፈናቀል ይገኙበታል ነው ያለው ድርጅቱ በመግለጫው።
እነዚህን ጉልህ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ለመከላከል በድርጅቱ ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ የተለያዩ አቤቱታዎችን እና ክሶችን የማቅረብ ሥራ እየሠራ ቢኾንም አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲሰፍን አሕጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ተቋማት ጫና እንዲያሳድሩም ድርጅቱ ጥሪ አቅርቧል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ዘንዘልማ ቀበሌ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በይፋ ተጀምሯል።
Next articleከ470 ሺህ በላይ ሰዎች የሚሳተፉበት የሰሜን ሸዋ ዞን የዚህ ዓመት የተፈጥሮ ሃብት ሥራ በንቅናቄ ተጀምሯል።