“ከጉስቁልና ለመውጣት የራሳችሁን ሰላም ጠብቁ” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

2
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከአዲስ ቅዳም ከተማ እና ከፋግታ ለኮማ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች እና በሰላም ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)፣ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኮር አዛዥ የኾኑት ብርጋዴር ጄኔራል አዲሱ መሐመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በሰላም እንዳንኖር አድርጎናል፤ የታጠቁ ኃይሎች በተለይም በገጠር አካባቢ ከልጆቻችን እየቀማ እየበላ እና እየዘረፈን ነው ብለዋል።
ሕዝብን ነጻ ለማድረግ በአንድነት መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል። በሚወሰደው የሕግ ማስከበር ሥራ ተባባሪ እንደሚኾኑ እና በራሳቸው አቅምም የታጠቀውን ኃይል እየታገሉ መኾናቸውን ገልጸዋል። በራሳችን አቅም ቀበሌያችንን ነጻ እያደረግን ነው ብለዋል።
አሁንም በየአካባቢው የሚንቀሳቀስ የታጠቀ ቡድን አለ፤ ይሄን ቡድን እየተከታተሉ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ነው ያሉት። የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኃይል እርምጃ ሊወስድ ሲንቀሳቀስ ቀድሞ መረጃ የሚያቀብል እና የታጠቀውን ቡድን የሚያሸሽ፣ ለታጠቀው ቡድን ስንቅ የሚያቀብል መኖሩንም ተናግረዋል።
መረጃ እና ስንቅ በሚያቀብሉት ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ገልጸዋል። በትግል የተጀመረው ትምህርት እንዳይቋረጥ ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የታጠቀው ቡድን የተሰማራው ለዘረፋ እንጂ ለሕዝብ ጥቅም አይደለም ብለዋል። አንድ ከኾን እና ለጋራ ሰላም ከተነሳን የሚያሸንፈን ታጣቂ ቡድን የለም ነው ያሉት።
በክልሉ ያለው ግጭት የውክልና እና የጠላት እጅ ያለበት ነው ብለዋል። ግጭቱ የጠላት ሴራ መኾኑን በመረዳት የጋራ ሰላምን ማረጋገጥ፣ የውስጥ አንድነትን ማጠናከር እና ለጠላት የማይመች ሀገር መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ለሀገር የሚጠቅመው ውይይት እና ንግግር መኾኑንም ተናግረዋል። የታጠቀው ቡድን ንጹሐንን በጭካኔ እየገደለ፣ እያገተ እና እየዘረፈ ነው፤ በጽንፈኛው ቡድን ተሰቃይተናል፤ ከዚህ በኋላ ይበቃናል ነው ያሉት።
የራሱን ችግር በራሱ የማይፈታ ሕዝብ በመከራ ውስጥ ይኖራል፤ ጠላቶቻችን የትውልድን ክፍተት እየተጠቀሙ ነው፤ የውስጥ አንድነትን በማጠናከር የኢትዮጵያን ክብር ማስጠበቅ፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው የሕዝባችን ፍላጎት ሰላም ነው ብለዋል። የጽንፈኛውን ግፍ እና በደል በቃኝ ብሏል ነው ያሉት። ከገጠመን የሰላም ችግር ለመውጣት እውነቱን አውጥተን በመወያየት መፍታት ያስፈልገናል ብለዋል።
ሕዝቡ ሰላምን ይፈልጋል፤ ከግጭት የሚጠቀሙ ደግሞ ሰላምን አይፈልጉም፤ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መታገል እና ለጋራ ሰላም የጋራ መፍትሔ ማስቀመጥ አለብን ነው ያሉት።
የችግሮቻችን መድኃኒት የሚገናኘው ከሐቀኛ ውይይት እና ከእውነት ላይ ነው ብለዋል። ሕዝብ በውስጡ ያለውን ታጣቂ ቡድን አሳልፎ ካልሰጠ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደማይችልም ገልጸዋል።
በታጣቂው ቡድን ላይ የጨከነ እና የመረረ አቋም እስካልያዛችሁ ድረስ ሰላማችሁን መመለስ አትችሉም ነው ያሉት። ከለቅሶ እና ከዋይታ ለማውጣት ገዳዩን ማውገዝ እና መታገል ይጠበቅባችኋል ብለዋል። ችግሩን በማድበስበስ ዘላቂ ሰላም እንደማይመጣም ገልጸዋል።
የሚዘርፋችሁን፣ የሚገድላችሁን፣ የሚያግታችሁን እና የሚያሰቃይችሁን ከእናንተ በላይ የሚታገለው የለም ነው ያሉት።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከለካያ ሠራዊት የኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አዲሱ መሐመድ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሕዝብ ጽንፈኛውን በመታገል ያሳየው ጀግንነት በታሪክ ሲታወስ ይኖራል ብለዋል። በጀግንነት አካባቢያቸውን ያላስደፈሩ መኖራቸውንም ገልጸዋል።
ጫካ የወጣው ቡድን ሕዝብን የሚያጎሳቁል መኾኑን ተናግረዋል። ሕዝብ ጽንፈኝነትን ሲቃወም እና ሲዋጋ ሰላምን ማረጋገጥ ይችላል ነው ያሉት። ታጣቂው ቡድን ንጹሐንን በግፍ የሚገድል፣ ሕጻናትን የሚያግት፣ የሃይማኖት አባቶችን አዋርዶ የሚገድል ነው ብለዋል።
ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጭ ያደረገ እና የታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪ መኾኑንም ገልጸዋል። ጀግና የሚፈጠርባትን፣ ጠላት የማይደፍራትን እና በነጻነት የኖረች ሀገርን ለጠላት አሳልፎ ለመስጠት የተነሳ ባንዳ መኾኑንም ተናግረዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የቆመው ለሕዝብ ሰላም እና ለሀገር ሉዓላዊነት መኾኑንም ገልጸዋል። ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ በታጣቂ ቡድኑ የመረረ አቋም ሊይዙ እና ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ሊቆሙ እንደሚገባ አመላክተዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የመጣነው ተመካክረን ያለውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ነው ብለዋል። የሰላም ባሕል የሌለው ኅብረተሰብ በጦርነት እና በግጭት ውስጥ እንደሚኖር ተናግረዋል። የሰላም ባሕልን ለመገንባት ተዘጋጁ ነው ብለዋል።
በግጭት ውስጥ መቆየት ለአዊ ብሔረሰብ ሕዝብ ታሪክ እና ባሕል እንደማይመጥንም ተናግረዋል። የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል። “ለታላቅ ሕዝብ ክብር የሚመጥነው እየመከሩ እና እየዘከሩ ሰላምን ማረጋገጥ ነው” ብለዋል።
ለሰላም የተዘጋጀ ሕዝብ ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ይሠራል ነው ያሉት። “ከጉስቁልና ለመውጣት የራሳችሁን ሰላም ጠብቁ”፣ የእናንተን ሰላም ከእናንተ በላይ የሚጠብቀው የለም ብለዋል።
የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለዘላቂ ሰላም እንዲሠሩም ጠይቀዋል። ለዘላቂ ሰላም ሐቀኝነት እና እውነተኝነት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የአካባቢው መሪዎች ራሳቸውን ከሰርጎ ገብነት በማራቅ ለሰላም እንዲሠሩም አሳስበዋል። በመንግሥት ቢሮ ተቀምጦ ጽንፈኝነትን በሚደግፍ አካል ላይ እርምጃ እንደሚወስዱም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሰላም በመመኘት ብቻ የሚገኝ አይደለም።
Next articleየፈተና ጥሪ ማስታወቂያ