
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለዳኞች፣ ለሬጅስትራሮች፣ ለችሎት ጸሐፊዎች እና ለስካኒግ ባለሙያዎች በኢ-ፋይሊንግ ሲስተም አጠቃቀምን በተመለከተ ሥልጠና ሰጥቷል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን ወጭ እና ጊዜ ቆጣቢ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከሚተገብራቸው የለውጥ ሥራዎች መካከል ኢ- ፋይሊንግ ሲስተም አንዱ ነው። በተለያዩ ሶፍትዌሮች የሚሠራው ሲስተሙ ተገልጋዮች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በአቤቱታ መዝገብ ለማስከፈት ያስችላቸዋል።
ወደ ክፍሎች እና ቦታዎች በሰው ይንቀሳቀሱ የነበሩ መዛግብትን በሲስተም መላላክ የሚያስችል አሠራር ነው።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው በሥልጠናው ማጠቃለያ ባስተላለፉት መልዕክት የዘመናዊ ዳኝነት አገልግሎት አማራጮች ዋና ዓላማ የተገልጋዩን እንግልት ወጭ እና ጊዜ መቀነስ ነው ብለዋል። ግልጽነት እና ተጠያቂነትን ማስፈን እንደኾነም ገልጸዋል።
የጀመርነው የኢ- ፋይሊንግ አገልግሎት ባለጉዳዮች ወደ ባሕር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃን፣ ደሴ እና ጎንደር ሳይሄዱ በቅርባቸው በሚገኙ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች መዝገብ ማስከፈት ያስችላቸዋል ነው ያሉት። በሲስተሙም ጉዳዩ ወደሚታይበት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይላካል ብለዋል።
አገልግሎቱ በ2019 ዓ.ም በማስፋት እና እስከ ወረዳ በማድረስ ተገልጋዮች ከእንግልት እና ወጭ በሚቀንስ አሠራር እንደሚተገበርም ገልጸዋል።
ኢ- ፋይሊንግ የወረቀት መዝገቦችን በዳኞች እና ባለሙያዎች እጅ ከማመላለስ ተላቅቆ ከእነጅ ንክኪ ነጻ በሆነ መልኩ በዲጂታል መንገድ መቀባበል ያስችላል ብለዋል።

የየደረጃው ዳኞች እና ባለሙያዎችም ለተጀመሩ አዳዲስ የአገልግሎት መስጫ አማራጮች ተግባራዊነት በትጋት እና በቅንነት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ፍርድ ቤቶች ዲጅታላይዜሽንን የሥራቸው አንድ አካል አድረገው መውሰድ እና በትብብር መሥራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከኢ ፋይሊንግ በተጨማሪ በቴክኖሎጅ የተደገፈ የርቀት ክርክርን እየተገበረ መኾኑን ገልጸዋል። በጎንደር፣ ደሴ፣ ደብረ ማርቆስ እና ደብረ ብርሃን ከተገነቡት ስማርት ችሎቶች በተጨማሪ በእያንዳንዳቸው ሁለት ስማርት ችሎቶች በመጠናቀቅ ላይ መኾናቸውን ጠቅሰዋል።
የቴክኖሎጅ ትግበራው ከሥራ ቦታችን ያፈናቅለናል፤ ሥራ ይቀንስብናል የሚል ስጋት ያላቸው ዳኞች እና ባለሙያዎች መኖራቸውን ጠቅሰው ስጋቱ ተገቢ አለመኾኑን ገልጸዋል።
ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይቶችን የሚያደርግ እና የፈጻሚዎች ሥልጠናንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
የዲጅታላይዜሽን ሥራው ለኅብረተሰቡ ከቀድሞው የተሻለ አገልግሎትን መስጠት ነው። ከምድብ ችሎት ወደ ባሕር ዳር የሚሄድ ተገልጋይም አይኖርም ነው ያሉት።
ከሰቆጣ፣ ከወልዲያ እና ከከሚሴ አካባቢ ወደ ደሴ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ምድብ ችሎቶች በአካል መሄድ ሳያስፈልጋቸው በአቅራቢያ ወደሚገኘዉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቴክኖሎጂውን በመጠቀም መዝገቦች እና አቤቱታ ማስከፈት እና ባሉበት ኾኖ መከራከር ይቻላል። ይህም የዜጎችን እንግልት የሚቀንስ ነው ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
ተገልጋዮች ትክክለኛ ዳኝነት የማግኘት እንጅ ጉዳያቸዉን ዳኛ የመምረጥ መብት እንደሌላቸው የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ዳኞች የሚሾሙት በግልጽ መስፈርት መኾኑን ገልጸዋል። ዳኞችን መድቦ የሚያሠራው ፍርድ ቤቱ ብቻ መኾኑን ተገንዘቦ አሠራርን አክብሮ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
“የሕዝብ እንግልትን ለመቀነስ የሚተገበሩ የለውጥ ሥራዎችን መደገፍ”፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ማገዝ እና ግልጽ ባልኾኑ ጉዳዮች መጠየቅ ይገባል ብለዋል።
አገልግሎቱን ላልተገባ የግል ጥቅም ሲባል ጣልቃ የሚገቡ እና የፍርድ ቤቱን ነጻነት የሚጋፉ አንዳንድ ባለሙያዎች ከተሳሳተ ተግባራቸው መቆጠብ እንዳለባቸውም አቶ ዓለምአንተ አሳስበዋል።
በቀጣይም ለዐቃቢያነ ሕግ፣ ለጠበቆች እና ነገረ ፈጆች እንዲሁም ለማረሚያ ቤት መሪዎች ሥልጠናው እንደሚሰጥም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
