“የግጭትን ጉዳት መርምሮ የተረዳ፣ ለሰላም ዋጋ ከፍሎ መሥራት አያቅተውም” አቶ ይርጋ ሲሳይ

5
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ መሪዎች ከወልዲያ ከተማ የንግዱ ማኅበረሰብ ጋር በሰላም እና ልማት ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ እንደ ክልል ያስተናገድናቸው ግጭቶች ተዘርዝሮ የማያልቅ ጉዳት አድርሶ አልፏል፤ በጋራ ቁሞ ዘላቂ ሰላምን መገንባት የግድ ነው ብለዋል። ከሁሉም በፊት ግጭት ያስከተለውን ጉዳት መርምሮ መረዳት ለሰላም በቁርጠኝነት ለመሥራት ያግዛል ሲሉም አስገንዝበዋል።
የጠላቶቻችን ሕልም ሁልጊዜም በግጭት እና ድህነት አዙሪት ውስጥ እንድንኖር ነው፤ ለዚህ ደግሞ ፊት ለፊት ቁመው ባይወጉንም የኛኑ ልጆች በፍርፋሪ ገዝተው እየላኩ ነው ብለዋል።
እውነትን ደፍሮ መነጋገር፣ የእነዚህን ታጣቂዎች ከሕዝብ ጥቅም የተቃረነ አሰላለፍ በግልጽ ተረድቶ መሞገት፣ ከተጨማሪ ጥፋት በፊት በሰላም ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱም መምከር እንደሚገባ አሳስበዋል። “የግጭትን ጉዳት መርምሮ የተረዳ ለሰላም ዋጋ ከፍሎ መሥራት አያቅተውም” ነው ያሉት።
በመንግሥት በኩል የሰላም በር ላይዘጋ ተከፍቷል” ያሉት አቶ ይርጋ ከሰላም እጠቀማለሁ የሚል ሁሉ ለዚሁ ሀሳብ ቁሞ እንዲደግፍ ጠሪ አቅርበዋል።
የጠላት አጀንዳ ተሸክሞ እየተላላከ እና በጥፋት መንገድ ውሎ ማደር የሚፈልግ እና ይህንን ሀሳብ የሚደግፍ ካለ ግን ለራሱም አይጠቀምም፤ ለሕዝብም የችግር ምንጭ ይኾናልና በጋራ እንከላከለዋለን ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝ ሰላምን ስለፈለግነው ብቻ አይገኝም፤ ይልቁንም በእውነተኛ መንገድ መኖር፣ ቤተሰብን በሰላም ማሥተዳደር፣ አካባቢንም ከሚያውክ ነገር መጠበቅ እና ለሀገርም ሰላም ተባባሪ ኾኖ መቆም ይገባል ነው ያሉት።
ገበያ ሰውን ይፈልጋል ያሉት አቶ ፍስሃ ነጋዴዎች ነግደው እንዲያተርፉ ወልዲያ ሰላም መኾን አለባት፤ ሰዎችም ለ24 ሰዓት ተዘዋውረው የሚገበዩባት እና የሚዝናኑባት እንድትኾን የጋራ ጥረት ማድረግ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
ነጋዴዎች ሰላምን ደግፈው ሲቆሙ ንግዳቸውን እንደሚደግፉ እና ሠርተው መለወጥን እያበረታቱ እንደኾነ ይቆጠራል ነው ያሉት። በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ ሰላምን ከሚያውኩ ጎን መቆም ግን ኪሳራን፣ ሞትን እና ጉስቁልናን እንደመምረጥ ይቆጠራል ብለዋል።
በመኾኑም የንግዱ ማኅበረሰብ ከወልዲያ ከተማ አሥተዳደር መሪዎቹ ጋር መመካከር፣ ችግሮችን በጋራ መፍታት፣ ሰላም የሚያውኩ አካላትን መክሮ መመለስ እና በሰላም ነግደው ሀብት በመፍጠር በሀገር አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪ መኾን እንዳለባቸው አቶ ፍስሃ መክረዋል።
የወልዲያ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ንጉሥ ዝናቡ ከተማዋ ሁነኛ የንግድ ማዕከል እና እንደ ሀገርም የስመጥር ነጋዴዎች መፍለቂያ መኾኗን ጠቁመዋል። የገጠመው የጸጥታ ችግር ግን የከተማዋን ልማት ጉዞ እየጎዳ ነው ብለዋል።
የታጠቁ ኃይሎች ነጋዴዎች ተዘዋውረው እንዳይሠሩ ከልክለዋል፤ ንብረታቸውን በየቦታው እያገቱ እና እየዘረፉም ችግር ሲፈጥሩ ቆይተዋል ነው ያሉት።
በነዋሪዎች ላይ አለመረጋጋት ለመፍጠር እና ንግድን ለማወክ ያሰቡ ጽንፈኞች ወደ ከተማዋ ሰርገው በመግባት ፍንዳታ ለመፍጠር ሲሞክሩም በየጊዜው እንደሚያዙ ጠቁመዋል። እንዲህ አይነት ኀላፊነት የጎደላቸው እና ሕዝብን የሚበድሉ ድርጊትችን በጋራ ቆሞ መከላከል እና ፍጹም ሰላማዊ ከተማ መፍጠር እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ወልዲያ ከተማ በኮሪደር ልማት የደመቀች እና ለኑሮ የተመቸች እንድትኾን ከተማ አሥተዳደሩ እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል። ሕዝቡም በተለይም ሰላሙን በመጠበቅ በኩል ተባባሪ እንዲኾን ምክትል ከንቲባው አስገንዝበዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች ወልዲያ ከተማ በኮሪደር ልማት እየተቀየረች እና ለነዋሪዎቿ ምቹ እየኾነች ነው ብለዋል። ማኅበረሰቡም ለልማቱ ተባባሪ ነው፤ ነጋዴዎችም በኮሪደር ልማት የሚነኩ ቦታዎችን በገዛ ፈቃዱ በማፍረስ እየተባበረ እንደኾነ ገልጸዋል። የከተማዋን ገጽታ ለመቀየር የሚሠሩ መሪዎቻቸውንም አመስግነዋል።
ይሁን እንጅ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ተዘዋውረው እንዳይነግዱ እንቅፋት እንደኾነባቸው ገልጸዋል። አማራ ክልል ትርፍ አምራች ነው፤ ይህንን ምርት አዘዋውሮ ለገበያ ለማቅረብ ችግር ኾኗል ነው ያሉት። ይህም ነጋዴዎች ነግደው እንዳያተርፉ፣ አምራቹ አርሶ አደርም የድካሙን ምንዳ እንዳያገኝ እየከለከለ ነው ብለዋል።
ጥያቄም ኾነ አለመግባባት በውይይት እንጅ በጦርነት አይፈታም ያሉት ነጋዴዎች የታጠቁ ኃይሎች መንግሥት ያመቻቸላቸውን የሰላም አማራጭ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሰላም ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ የጋራ ድል ነው።
Next articleከ24 ሺህ በላይ ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ሥራ እና ክህሎት መምሪያ አስታወቀ።