
ጎንደር: ታኅሣሥ 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአንድ እስከ አምስት ገዳይ ተብለው ከተቀመጡ በሽታዎች መካከል አንዱ ስትሮክ ወይም በጭንቅላት ውስጥ በድንገት ደም መፍሰስ እና መቋረጥ ነው።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሕክምናቸውን ሲከታተሉ ያገኘናቸው ወይዘሮ ታድላ ፀሐይ ግማሽ ፊታቸዉ መደንዘዝ፣ ማዞር፣ የጆሮ መሰቅሰቅ ሕመም ሲሰማቸው ወደ ሕክምና ተቋም ይሄዳሉ። ሲመረመሩም የስትሮክ በሸታ እንደኾነ አወቁ። ወደ ሕክምና ተቋም ቶሎ በመምጣታቸው በባለሙያዎች ድጋፍ እና ክትትል በማግኘታቸው ከገጠማቸው የስትሮክ ሕመም ለውጥ እያዩ እና እየተሻላቸው መኾኑን ነግረውናል።
ሌላው ሕክምናቸውን ሲከታተሉ ያገኘናቸው አቶ ጀግናው አየልኝ እጅ እና እግራቸው መፍዘዝ እና መዛል ስሜት እንደነበረና ወደ ሐኪም ቤት ሲመጡ ስትሮክ እንደኾነ ተነገራቸው። ወዲያውኑ የሕክምና ክትትል በማድረግ እና በሐኪሞች የታገዘ የአካል እንቅስቃሴ በማደረግ መራመድ መቻላቸውን ተናግረዋል።
አስተያየት ሰጭዎቹ ከጤና በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሌለው ገልጸው ሌሎች ሰዎች በበሽታው ከመጠቃታቸው በፊት ወደ ሕክምና ተቋማት መሄድ መመርመር እንዳለባቸው መክረዋል።
በሽታው በድንገት ግማሽ የሰውነት ክፍል መዛል፣ መፍዘዝ፣ ከባድ ራስ ምታትና የእይታ ችግርን ጨምሮ ሌሎች ዋና ዋና ምልክቶችን እንደሚያሳይ ያብራሩት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የነርቭ ትምህርት ክፍል ኀላፊ እና የነርቭ ስፔሻሊስት ሐኪም ዶክተር አበበ ገላው ናቸው።
በጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ እና መቋረጥ ወይም የስትሮክ በሽታ የመርሳት ችግርን ያመጣል፤ አካላዊ ጉዳትን በማስከተልም ለሞት ይዳርጋል ያሉት ዶክተር አበበ ችግሩ ባጋጠመ በአራት ሰዓት ጊዜ ውስጥ በፍጥነት ወደ ሕክምና ተቋም በመሔድ ሕክምና ማግኘት እንደሚገባ ይመክራሉ።
በጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ እና መቋረጥ ወይም የስትሮክ በሽታ እንዲከሰት ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል የልብ ሕመም፣ የደም ግፊት፣ የስኳር ሕመም፣ እንቅስቃሴ አለማድረግ እና ከመጠን ያለፈ ክብደት ዋና ዋናዎቹ መኾናቸውን ዶክተር አበበ አመላክተዋል።
የስትሮክ ሕመምን ቀድሞ ለመከላከል በቂ እንቅልፍ ማግኘት፣ ስኳርን እና የደም ግፊትን መቆጣጠር፣ እንቅስቃሴ ማድረግ እና ከሱስ መራቅ እንደሚገባ ዶክተር አበበ አስገንዝበዋል።
ማኅበረሰቡ በጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ እና መቋረጥ ወይም የስትሮክ በሽታን መነሻ ምክንያት እና የሚያደርሰውን ከፍተኛ የኾነ የጤና እክል በመገንዘብ ጤናን መጠበቅ ይገባልም ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ማርታ አዱኛ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
