“ምሁራን ካስተማራቸው ሕዝብ ጎን ቁመው ለሰላም እና ልማት መሥራት ያለባቸው ሰዓት አሁን ነው” አቶ ይርጋ ሲሳይ

3
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ መሪዎች “ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የልሂቃን ድርሻ” በሚል መሪ መልዕክት ከወልድያ ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና የአሥተዳደር ሠራተኞች ጋር ተወያይተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝ፣ የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ እና ሌሎችም የክልሉ እና የዞን መሪዎች ተገኝተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ የአማራ ክልልን የልማት ጉዞ የሚያቀጭጭ ግጭት ገጥሞ መቆየቱን ገልጸዋል። ይህም የክልሉን ትምህርት ክፉኛ ጎድቶ ማለፉን አንስተዋል። መንግሥት ሕዝብን በማቀናጀት ባደረገው ርብርብ የታቀደውን የከፋ ነገር ማስቀረት ስለመቻሉም ጠቁመዋል።
በርካታ ታጣቂዎችም ወደ ሰላም እየተመለሱ በመኾኑ ተቸግሮ የነበረውን ሕዝብ እፎይታ መስጠት ተችሏል ብለዋል። ይህም መንግሥት በተከተለው ሆደ ሰፊነት ጠንካራ የሰላም ፍላጎት የመነጨ ነው ብለዋል።
አሁንም ቢኾን የክልሉን ሕዝብ እረፍት ለመንሳት የሚላላኩ አሉም ብለዋል። እነዚህን አካላት በጋራ ለመምከር እና ሀገር እና ሕዝብን ከሚጎዳ ሀሳባቸው ለማላቀቅ የምሁራን ድርሻ መኾኑንም ተናግረዋል።
ሕዝብ ተቸግሯል፤ ሰላም ናፍቆታል፤ ሰላሜን መልሱልኝ እያለም በየአደባባዩ እየተናገረ ነው ብለዋል። ምሁራንም ካስተማራቸው ሰላም ናፋቂ ሕዝብ ጎን ይቁሙ፤ ለሰላም እና ልማቱ በመሥራትም ውለታ መላሽነታቸውን ያረጋግጡ፣ ለዚህ ደግሞ ሰዓቱ አሁን ነውና በዝምታ መዋል እና ማደር የለባቸውም ሲሉም አስገንዝበዋል።
ከድህነት እና ግጭት ለመውጣት ምክክር ወሳኝነት እንዳለውም ገልጸዋል። መንግሥት የትኛውም አይነት ችግር በንግግር እና በውይይት እንዲፈታ እየሠራ ነው፤ ምሁራን መነጋገር እና ለወቅታዊ ችግሮች ዘላቂ መፍተሔዎችን ማመንጨት አለባቸው ብለዋል።
የገጠመው የጸጥታ ችግር ምሁራንም ራሳቸው ለሥራም ኾነ ለቤተሰብ ጥየቃ እንደልብ እንዳይንቀሳቀሱ ገድቧል ነው ያሉት። ምሁራን ያስተማራቸው ሕዝብ ለገጠመው ችግር የመፍትሔ አካል የመኾን ጊዜው አሁን ነው፤ ይህን ችግር እንዲፈታ ከመጣር ይልቅ ቁመው ማየት አይበጅም፤ የችግሩን ምንጭ በጥናት መለየት እና መፍትሔውንም እያመላከቱ በጋራ መሥራት ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝ “ምሁርነት ሚዛናዊነት ነው፤ ዕውቀትን ተጠቅሞ መፍትሔ አፍላቂነት ነው” ብለዋል። በተለይም በሀገር እና ሕዝብ ላይ ችግር በገጠመ ጊዜ ዛሬ ላይ ቁሞ ነገን በመመልከት ችግሮችን ለመፍታት በቂ ልምድ መያዝ፣ በተግባርም መሥራት ከምሁራን ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል።
እንደሀገር ወንድማማቾች በጋራ እንዳይኖሩ የሚያደርጉ አፍራሽ ትርክቶች ተዘርተዋል። ይህም ዛሬ ግጭቶችን እንድናስተናግድ አድርጓል፤ ዋጋም አስከፍሏል ነው ያሉት አቶ ፍስሃ።
መንግሥት አፍራሽ ትርክቶችን እያስተካከለ እንደዓድዋ ሙዚየም አይነት የጋራ ምልክቶቻችንን ደግሞ በተግባር እየገነባ ነው ብለዋል። ምሁራንም አፍራሽ ትርክቶችን የሚያስተካክሉ፣ ለሰላምም በር የሚከፍቱ አሻጋሪ ሀሳቦችን በማመንጨት የበኩላቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ሞክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ ምሁራን ችግር ፈች የኾኑ ጥናት እና ምርምሮችን በመሥራት ለክልሉ እና ለሀገር የሚበጁ የሰላም መፍትሔዎችን ማመንጨት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። “ምሁር ሊነግረን የሚገባውን ነገር ንግሩን፤ እየወሰድን በመተግበርም ሕዝብን ለማገልገል እንሠራበታለን” ነው ያሉት።
የውይይቱ ተሳታፊ ምሁራንም ታጣቂዎች ወደ ጫካ የወጡት የአማራ ክልል ጥያቄዎችን አስፈታለሁ ብለው ነበር፤ አሁን ላይ ግን በግጭት ሰበብ ሕዝብ እየተበደለ ነው ብለዋል። በታጣቂዎች የሚደረግ እንቅስቃሴ በአማራ ክልል ብቻ ሳይኾን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች መኖሩ እንደሀገር ጥፋቱ የከፋ ስለመኾኑም አመላክተዋል።
በተፈጠረው ችግር ምሁራንም ተጠቂዎች መኾናቸውን አንስተዋል። ይህንን ለመፍታትም በጥናት እና ምርምር የተደገፉ የመፍትሔ ሀሳቦችን ለማመንጨት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ግጭቶች ተፈትተው አማራ ክልል እና ሀገሪቱም ሰላም እንዲኾኑ ሁሉም ኀላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣም ምሁራኑ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
ግጭቶች ተፈትተው እንደሀገር ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም በአንድነት በመቆም መሥራት አለበት ብለዋል። አፍራሽ የኾኑ መገፋፋቶች እና አቀራራቢ ያልኾኑ ንግግሮች ቁመው ልባዊ ውይይቶች ይቀጥሉ ነው ያሉት።
ለግጭቶች ሰበብ ተደርገው የሚነሱ የመልማት ጥያቄዎችም በኮታ ሳይኾን እንደ የአንገብጋቢነታቸው ተለይተው ምላሽ እንዲሰጣቸው ምሁራኑ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መልእክት፦
Next article“ከትምህርት የራቀ ትውልድ ከድህነት አዙሪት ሊወጣ አይችልም” አቶ ካሳሁን አዳነ