
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከቲሊሊ ከተማ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።
በውይይቱ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)፣ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አዲሱ መሐመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በተደጋጋሚ ሕዝባዊ ውይይት እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል። ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ መወያየት፣ መመካከር እና የጋራ መፍትሔ ማመላከት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የአማራ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት በጸጥታ ችግር ውስጥ መቆየቱን ተናግረዋል። ችግሮችን በኃይል እፈታለሁ የሚል ኃይል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ብዙ ጉዳት መድረሱን ነው የገለጹት። የሰላም ትሩፋቶችን ማግኘት ሲገባን፣ የግጭት ገፈት ቀማሽ ኾነን ቆይተናል ነው ያሉት።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሕዝብ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ከመንግሥት ጋር በመኾን ያደረገው አስተዋጽኦ ታሪካዊ እና ለሌሎች አካባቢዎችም ተሞክሮ የሚኾን ነው ብለዋል።
ችግሮችን በብልሃት መፍታት ነባር ባሕል እና እሴት ካለው ሕዝብ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። ችግሮች የሚፈቱት በስክነት፣ በብልሃት እና በመተማመን ነው ብለዋል። በአካባቢው ያለው አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ እና አስተማማኝ እንዲኾን መከባበር፣ መመደማመጥ፣ መወያየት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
“መመካከር እና መወያየት ለሰላም እሴት ግንባታ አስኳል መኾኑን” ገልጸዋል። ባለፉት ዓመታት በግጭት ካጣነው ጉዳይ መማር፣ መቆጨት እና ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የባሕል፣ የእሴት እና የወግ መሸርሸር መፍጠሩንም ተናግረዋል። የዳበረ ባሕል፣ እሴት እና ወግ ካለው ሕዝብ የማይጠበቁ ድርጊቶች መፈጸማቸውንም ተናግረዋል።
ለሀገር በቀል እውቀት ክብር ያለመስጠት ችግር ተፈጥሯል፤ ስለ ሰላም የሰበኩ የሃይማኖት አባቶች ተንበርክከው ተገርፈዋል፤ ተገድለዋል ነው ያሉት።
ይህ ደግሞ ለነገው የእሴት ግንባታ አሉታዊ አስተዋጽኦ የሚያደርግ መኾኑን ተናግረዋል። ለነገ ትውልድ ግንባታም የከፋ ጠባሳ እንደሚያሳድር ነው የገለጹት። በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ንብረት ወድሟል ነው ያሉት።
የአገልግሎት፣ የምርት እና የሰው እንቅስቃሴ መገደቡንም ተናግረዋል። የእንቅስቃሴ መገደብ ደግሞ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ እና ማኅበራዊ መስተጋብር እንዳይኖር ያደርጋል ነው ያሉት።
ባለፉት ዓመታት የሰበዓዊ ልማት ግንባታ ችግር እንደገጠው የተናገሩት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ባለፉት ዓመታት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል፤ ይህ ደግሞ ነገ መፍትሔ የሚያመላክቱ ምሁራን፣ የሚያክሙ ሐኪሞች፣ የሚያስተምሩ መምህራን አይኖርም ማለት ነው ብለዋል።
የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በፍጥነት ካላስተካከልነው ዳፋው የከፋ ይኾናል ነው ያሉት። ግጭቱ የክልሉ ውስጣዊ አንድነት እንዲሸረሸር፣ ሕዝብ የሥነ ልቦና ጫና እንዲደርስበት ኾኗል ነው ያሉት። ሕዝብ በሥነ ልቦና ሲጎዳ ደግሞ በቀላሉ ተጠቂ ይኾናል፤ ለልማት እና ብልጽግና ያለው ተነሳሽነትም ይቀንሳል ብለዋል።
የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ባለሃብቶች ለቀው እንዲወጡ በክልሉ እንዳያለሙ አድርጎ መቆየቱን ተናግረዋል። ችግሮች ከዚህ በላይ እንዳይሰፉ በመወያየት ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ለዘላቂ ሰላም እውነተኛ እና ሐቀኛ ውይይት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
