የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የዲጂታላይዜሽን ጉዞ በከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተጎበኘ።

8
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣የኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ እና የኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ኸይረዲን ተዘራ (ዶ.ር) እንዲሁም ሌሎች የክልሉ የሥራ ኀላፊዎች በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የተከናወኑ የዲጂታላይዜሽን እና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተመልክተዋል።
ጉብኝቱ የፖሊስ አገልግሎትን ለማዘመን እና የወንጀል መከላከል ሥራን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ያለመ ነው።
የክትትል ካሜራዎችን እና ዘመናዊ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም የክልሉን ሰላም የማስከበር ሥራን፣ በከተሞች እና ቁልፍ ቦታዎች ላይ የሚደረጉ የጸጥታ ክትትል ሥራዎች በቴክኖሎጂ የታገዙ ስለመኾናቸው የሥራ ኀላፊዎች ተመልክተዋል።
በተጨማሪም ዲጂታል መረጃ አያያዝን፣ የወንጀል መዝገቦችን እና የተጠርጣሪዎችን መረጃ በዘመናዊ ዳታቤዝ የማደራጀት ሥራን እንዲሁም ፈጣን አገልግሎት በመስጠት የሕዝብን ደኅንነት ለመጠበቅ እና ለጥሪዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የተዘረጉ መሰረተ ልማቶችን እና ቁልፍ የቴክኖሎጂ ሥራዎችን ነው በጉብኝቱ ወቅት የሥራ ኀላፊዎቹ የተመለከቷቸው።
የሥራ ኀላፊዎቹ በጉብኝታቸው ወቅት እንደገለጹት የፖሊስ ተቋም ራሱን በቴክኖሎጂ ማዘመኑ ወንጀልን በሳይንሳዊ መንገድ ለመከላከል እና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም ይኾናል ብለዋል።
በክልሉ ፖሊስ እየተከናወኑ ያሉ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎች አበረታች መኾናቸውንም የጉብኝቱ ተካፋዮች አክለው ገልጸዋል።
የፖሊስ ተቋም ራሱን በቴክኖሎጂ ማዘመኑ ወንጀልን አስቀድሞ ለመከላከል እና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ሲሉ በጉብኝቱ የተገኙ የሥራ ኀላፊዎች አረጋግጠዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ.ር) በበኩላቸው የተጀመሩ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች የሰው ኀይልን በብቃት ለመምራት እና የአገልግሎት አሰጣጥን ግልጽነት፣ ተጠያቂነት ባለው መልኩ ለማከናወን የሚያስችሉ መኾናቸውን አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል መከላከል እና ምርመራ ሥራውን በዲጂታል በማዘመን ከፌደራል የጸጥታ አካላት ጋር ግንኙነቱን አጠናከሮ ሥራዎችን በመሥራት በዘመናዊ ዲጂታል ሥርዓት ማዕቀፍ ውስጥ የበኩሉን ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ ከአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሕገ ወጥ የፀረ ተባይ እና የአፈር ማዳበሪያ ዝውውሮችን መግታት ይገባል።
Next article“መመካከር እና መወያየት ለሰላም እሴት ግንባታ አስኳል ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)