
አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ከጠባቂነት ወጥታ ስንዴን ወደ ውጭ መላክ የጀመረችበትን ስኬት የሚያስቃኝ ዘጋቢ ፊልም ተመርቋል።
“የኢትዮጵያ የስንዴ ትራንስፎርሜሽን” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም በአሜሪካ ሎሳንጀለስ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የፊልም ባለሙያዎች የተዘጋጀ እና ሀገሪቱ በአፍሪካ ግብርናን በማዘመን እና ራስን ለመቻል የምታደርገውን ስኬታማ ተግባር የሚያሳይ ፊልም ነው የተመረቀው።
ኢትዮጵያ በበጋ መስኖ የስንዴ ልማት አብነት የሚኾኑ ውጤታማ ተግባራትን እያሳካች እንደሆነ በፊልም ምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተነስቷል።
በኦሮሚያ፣ በአፋር እና በአማራ ክልሎች ያለውን የስንዴ ምርት ስኬት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን የመቻል አቅም የሚያሳይ እና ገጽታን የሚገነባ ፊልም መኾኑን የተናገሩት የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ.ር) ናቸው።
በአፍሪካ ታላቅ የስንዴ አምራች ሀገር የኾነችው ኢትዮጵያ ይህንን ጥልቅ የኾነ ትራንስፎርሜሽን በምታከናውንበት በዚህ ወቅት ፊልሙ ጥራቱን ጠብቆ የተሠራ እና ለዓይን የሚማርኩ የኢትዮጵያ እርሻዎች፣ የአዝመራ አሰባሰብ ሂደቶች እና የአርሶ አደሮች የደስታ ስሜትንም ያካተተ ነው ብለዋል።
የዘጋቢ ፊልሙ ታሪክ በሦስት ዋና ዋና ምዕራፎች ላይ ያተኮረ እና ኢትዮጵያ ለዓመታት ለስንዴ ግዥ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ይዳስሳል ነው ያሉት። ይህን ለመቀየር የፖለቲካ ቁርጠኝነት የታከለበት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እንዴት እንደተጀመረ እንዲሁም አርሶ አደሮች እንዴት በኩታ ገጠም እርሻ እንደተሰለፉ የሚያስቃኝም ነው።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ.ር) በቁርጠኝነት ተግባራዊ የተደረገው የኩታ ገጠም እርሻ አሠራር ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን እና በአሲዳማነት የተጠቁ በርካታ ሄክታር መሬቶችን በኖራ በማከም ወደ ምርት እንዲገቡ የማድረግ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።
ፊልሙ ስለ ስንዴ ከመተረክም በላይ ጽናትን፣ ፈጠራን እና ራስን ወደ መቻል እና ወደጋራ ብልጽግና የምትገሰግስን ሀገር የሚያሳይ ምስል እንደኾነ ነው የገለጹት።
ዘጋቢ:- ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
