
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢፌዴሪ የሰላም ሚኒስቴር እና በአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ትብብር “ማኅበራዊ ሀብቶቻችን ለዘላቂ ሰላም እና ለኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን” በሚል መልዕክት ከክልሎች ከተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ጋር ምክክር እየተደረገ ነው።
በምክክሩ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ ኢትዮጵያ በብዙ ፈተናዎች ተፈትና ፈተናዎችንም በመመካከር የተሻገረች ሀገር መኾኗን ገልጸዋል።
ልዩነት በማኅበረሰብ ውስጥ የማይቀር መኾኑን ያነሱት ሚኒስትሩ ልዩነቶችን በምክክር መፍታት ደግሞ የኢትዮጵያውያን ባሕል መኾኑን ገልጸዋል።
ይሁን እንጅ ነባር ሀገር በቀል እሴቶች እየተሸረሸሩ በመምጣታቸው ባለፉት ዓመታት ሀገሪቱ በግጭት አዙሪት ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል ብለዋል።
ችግሮቹን በሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶች ለመፍታት እንደ ሀገርም ከ75 በላይ የዳበሩ እሴቶች ላይ ትኩረት ተሠጥቶ እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት። ከዚህ በፊት በተሰሠራው ሥራ አንጻራዊ ሰላም መምጣቱን አንስተዋል።
አሁን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ተሟላ ሰላም እንዲመለስ ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ምክክሮች እየተካሄዱ ነው። የሀገር ሽማግሌዎች እየሠሩት ያለውን ሥራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ እንዳሉት የአማራ ክልል ሕዝብ የተከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ምክክርን እንደ ትልቅ ባሕል አድርጎ የዘለቀ ሕዝብ ነው። የበደለን ወቅሶ፣ የተበደለን ክሶ ይቅር መባባልን የክልሉ ባሕል እንደኾነም ነው የገለጹት።
ባለፉት ዓመታት የተከሰተውን ችግር ለመፍታትም የሀገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል። የሀሳብ ልዩነት ሁሌም የሚኖር እና የሚቀጥል መኾኑን ያነሱት አፈ ጉባኤዋ የሚነሱ ችግሮችን ደግሞ በምክክር መፍታት ይገባል ብለዋል።
የሽምግልና ሥርዓቱ የጠነከረ መሠረት እንዲኖረው መንግሥት የሕግ እውቅና እንዲያገኝ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
የሀገሪቱ ልማት እና ሰላም በጽኑ መሠረት ላይ እንዲቆም የሀገር ሽማግሌዎች የጀመሩትን ሥራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
ተደራሽነቱንም እንዲያሳድጉም ጠይቀዋል። የታጠቁ ቡድኖችም ችግሮቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ዳግማዊ ተሰራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
