ባለብዙ ተዋናይ የግብርና ኤክስቴንሽን ስልት ረቂቅ አዋጅ ውይይት እየተደረገበት ነው።

9
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በሀገር አቀፍ የተዘጋጀውን የባለብዙ ተዋናይ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት አሰጣጥ እና አሥተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ የሕዝብ አስተያየት መድረክ አካሂዷል።
በውይይቱ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ የቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ባለድርሻ አካላት እና አርሶ አደሮች ተገኝተዋል።
ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ የግብርና ኤክስቴንሽን ስልቱ ለረጂም ጊዜ የቆየ ነው ብለዋል። የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም፣ በዘርፉ ላይ ባለሀብቶችም እንዲሳተፉበት እድል በመስጠት፣ ሕጋዊ ለማድረግ እና ልማትን በኢንቨስትመንት ለማጠናከር ሕጉ መሻሻል ማስፈለጉን ገልጸዋል።
ለግብርናው ዘርፍ ትኩረት መሰጠቱ እና የሕዝቡን ፍላጎት የማካተት ተገቢነት በተጨማሪነት ጠቅሰዋል። በርካቶች የሚሳተፉበት የግብርና ዘርፍ መፍጠር ለልማቱ ተጠቃሚነት እና ዘላቂነት እንደሚያግዝ ነው የገለጹት።
የውይይቱ ዓላማም የባለድርሻ አካላት እና የዘርፉ ተዋንያንን ሀሳብ ለማካተት እና በቀጣይም በባለቤትነት ስሜት እንዲተገብሩት መኾኑንም ጠቅሰዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ደረጀ ማንደፍሮ በመንግሥት ብቻ ሲሰጥ የቆየውን የግብርና ኤክስቴንሽን ወደ ባለብዙ ተዋናይ አገልግሎት እና አሥተዳደር ለመቀየር በረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
አዲሱ የኤክስቴንሸን አገልግሎት ሥርዓት የግል ዘርፉ፣ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት እና የሙያ ማኅበራትን ያሳትፋል።
በቴክኖሎጂ የተደገፈ እና ተጠያቂነት ያለው አሠራር በመዘርጋትም የገጠር ሁለንተናዊ ለውጥን እውን እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በረቂቅ አዋጁ፦
👉የአገልግሎት አቅራቢዎች ምዝገባ እና ብቃት፤
👉የኤክስቴንሽን አገልግሎት (የቴክኖሎጂ ማስተዋወቅ፣ የቢዝነስ ማማከር፣ የሥልጠና አገልግሎት፣ የገበያ ትስስርን፣ የፋይናንስ አቅርቦትን ስለማቀናጀት)፤
👉 የዲጂታል ግብርና ኤክስቴንሽን፤
👉 የፋይናንስ ምንጭ እና ፈንድ፤
👉 የክፍያ አሠራርን፤
👉 አካታችነት እና ተጠያቂነትን በተመለከተ እንደተካተተ ገልጸዋል። በውይይቱ የፌደራል መንግሥት ረቂቅ አዋጁ ይዘት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የገቢ አሰባሰብን ጨምሮ የበጀት ዓመቱን እቅዶች ከምርጫ በፊት ለመፈጸም እየተሠራ ነው።
Next articleየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለባለ አነስተኛ ይዞታ እና ተደራጅተው ለሚሠሩ አርሶ አደሮች የግብርና ብድር አገልግሎትን ይፋ አደረገ።