
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በቴክኖሎጂው ዓለም ቻትጂፒቲ እና መሰል የሰው ሠራሽ አስተውሎት መተግበሪያዎች የዕለት ከዕለት ሕይወታችን አካል እየኾኑ መጥተዋል። ኾኖም ግን እነዚህ መተግበሪያዎች ድካማችንን ከማቅለል ባለፈ በአዕምሯችን ላይ ምን እያደረሱ ነው ብለው ጠይቀው ያውቃሉ?
በቅርቡ በማሳቹሴት የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (MIT) የተካሄደ አዲስ ጥናት አስገራሚ እና አስደንጋጭ ውጤት ይዞ ወጥቷል። ጥናቱ እንደሚያመለክተው የሰው ሠራሽ አስተውሎትን የጽሑፍ ይዘት ለማመንጨት አዘውትረን የምንጠቀም ከኾነ የእውቀት ዕዳ (Cognitive Debt) ለተሰኘ ችግር እንደምንጋለጥ ያስረዳል።
ይህ ማለት ሥራችንን በሚገርም ፍጥነት እና ጥራት ቢያቀላጥፍልንም የአዕምሯችንን የማሰብ አቅም በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳል ሲል ጥናቱ ያስጠነቅቃል።
በጥናቱ የምርምር ሂደት የተሳተፉ አካላት በሦስት ቡድን የተከፈሉ ሲኾን ቻትጂፒቲን የሚጠቀሙ፣ በጉግል ማሰሻ የሚጽፉ እና አዕምሯቸውን ብቻ በመጠቀም የጽሑፍ ይዘት የሚያመነጩ ናቸው።
በእነዚህ ሦስት ቡድኖች ላይ የተደረገው ጥናት ያስገኘው ውጤትም የሚያሳስብ ነው። በሰው ሠራሽ አስተውሎት ታግዘው የጻፉ ተሳታፊዎች የአንጎል የሥራ ንቁነት (Brain Connectivity) እስከ 55 በመቶ ቀንሶ ተገኝቷል። እነዚህ ሰዎች በሰው ሠራሽ አስተውሎት ታግዘው ስላዘጋጁት ጽሑፍ አንድ ነጠላ ዓረፍተ ነገር እንኳን ማስታወስ አቅቷቸዋል። ከአስር ተሳታፊዎች መካከል ስምንቱ (83 በመቶ) የጻፉትን ነገር ፈጽሞ ሊያስታውሱ አልቻሉም። ይህ የሚያሳየው አዕምሯችን በቴክኖሎጂው ላይ ብቻ ጥገኞች እየኾንን መምጣታችንን ነው ሲል ጥናቱ ጠቁሟል።
በእኛ ላይ የፈጠረው ተጽዕኖ ወይም ጥናቱ ‘የእውቀት ዕዳ’ ብሎ የገለጸውን ችግር የምንረዳው መተግበሪያውን መጠቀም ስናቆም እንደኾነም ተመላክቷል።
መጀመሪያ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ሲሠሩ የነበሩ ተማሪዎች በኋላ ላይ ያለ መተግበሪያ በራሳቸው አቅም እንዲጽፉ ሲደረጉ በፊትም በራሳቸው አቅም ይጽፉ ከነበሩት ተማሪዎች እጅግ በጣም ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይተዋል።
ይህም ማለት ሰው ሠራሽ አስተውሎትን አብዝቶ መጠቀም አእምሯችንን ደካማ እና ለፈጠራ ሥራ ዝግጁ እንዳይኾን እንደሚያደርገው በጥናቱ ድምዳሜ ላይ ተደርሷል፡፡ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚዘጋጁ ጽሑፎችም ቢኾኑ የተለየ የፈጠራ ለዛ የሌላቸው እና ተመሳሳይነት የሚበዛባቸው ኾነው ተገኝተዋል።
ጥናቱ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ፈጽሞ መጠቀም አያስፈልግም የሚል ድምዳሜ ያለው ሳይኾን በእነዚህ መተግበሪያዎች ጥገኛ ሳንኾን ሀሳብ ለማመንጨት እንደ ረዳት ብቻ መጠቀም እንደሚገባ ይመክራል፡፡
አዕምሯችን የፈጠራ አቅሙን እንዳያጣ በየቀኑ ያለ ምንም የቴክኖሎጂ ድጋፍ የምናስብበት እና የምንጽፍበት ጊዜ ሊኖሩን ይገባል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
