
ጎንደር: ታኅሣሥ 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የማዕከላዊ ጎንደር ዞን “ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት ከምዕራብ ደምቢያ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ፣ የዞኑ የሥራ ኀላፊዎች እንዲሁም የወረዳው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
የክልሉ የጸጥታ ችግር በውይይት እና በንግግር እንጂ በመሣሪያ የማይፈታ መኾኑን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። በመኾኑም ለሰላም ሁሉም በመዘጋጀት ሰላምን ማፅናት እንደሚገባ ገልጸዋል። ሰላም እንዲመጣ ተማጽነዋል። መንግሥት ሕግ እንዲያስከብርም ጠይቀዋል።
መንግሥት በወረዳው የሚገኘውን ጎርጎራ ኢኮ ሪዞርትን በማልማት ለጎብኝዎች ክፍት ቢያደርግም የሰላም እጦቱ ከልማቱ ተጠቃሚ እንዳይኾን እንቅፋት ፈጥሯል ብለዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ የሰላምን አማራጭ የተቀበሉ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም እንደ ዞን እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
መንግሥት በሆደ ሰፊነት የሰላም አማራጭ ሲያቀርብ መቆየቱን ያነሱት አሥተዳዳሪው ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ እና በምኅረት እንዲገቡ በቁርጠኝነት መሥራት ከማኅበረሰቡ ይጠበቃል ብለዋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዥ ኮሎኔል ዘሪሁን ተረፈ ሰላም የሚመጣው በመከላከያ ሠራዊት ብቻ ሳይኾን በሁሉም ተሳትፎ በመኾኑ ለሰላም የበኩላችሁን ድርሻ ልትወጡ ይገባል ነው ያሉት።
የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሰላምን ለማጽናት በትኩረት ልትሠሩ ይገባልም ብለዋል። የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ ለኢትዮጵያ ሕልውና ስንል ይቅርታን ማስቀደም እና አንድነትን ማጽናት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
መንግሥት በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ኾኖ ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል። በገጠር እና በከተማ የኮሪደር ልማቶችን በማስፋት ሀገርን ለመቀየር እየሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
መንግሥት የማዳበሪያ፣ የነዳጅ እና የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ እና ወደ ሥራ በመግባት የኢትዮጵያን ከፍታ ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑንም ምክትል ቢሮ ኀላፊው ጠቅሰዋል።
በክልሉ ከ15 ሺህ በላይ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪን በመቀበል የተሐድሶ ሥልጠና መውሰዳቸውን አንስተው መንግሥት በምኅረት የገቡ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ ማከናወኑን አብራርተዋል።
የሰላም ጥሪው ውጤታማ እንዲኾን የወረዳው ነዋሪዎች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
