
ሰቆጣ፡ ታኅሣሥ 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “ሁሌም ለሰላም ዘብ እንቆማለን” በሚል መሪ መልዕክት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጋዝጊብላ ወረዳ በከፍተኛ የሀገር መከላከያ መኮንኖች የተመራ የሰላም ኮንፈረንስ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ተካሂዷል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰላም እጦት ምክንያት የተዘጉ ትምህርት ቤቶች በወረዳ መኖራቸውን ገልጸዋል። ወላጆች የልጆቻቸውን የወደ ፊት ህልም ለማስቀጠል ሰላምን መደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል። ክልሉ ከገባበት የሰላም እጦት ለማውጣት መምከር ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ሰላምን ማስፈን የሚቻለው በጦርነት ሳይኾን በውይይት ነውም ብለዋል። ሁሉም የድርሻውን ካልተዋጣ በመከላከያ ሠራዊት ብቻ ሰላም ማምጣት አይቻልም ነው ያሉት። ውስጣዊ ልዩነቶቻችንን በውይይት መፍታት ያስፈልገናል ሲሉ ተናግረዋል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ምክትል አሥተዳዳሪ ሹመት ጥላሁን ባለፉት ዓመታት የነበሩ የሰላም እጦቶች የአማራን ሕዝብ ኢኮኖሚ እና ልማት ያወደመ እንጂ ያለማ አይደለም ብለዋል ። ይህንን ተግባር ማውገዝ የሀገርን ልማት እና እድገት መደገፍ ነው ያሉት ምክትል አሥተዳዳሪው በጋዝጊብላ ወረዳ ያለውን አንጻራዊ ሰላም ለማጽናት በጋራ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በመድረኩ የተገኙት የሰሜን ምስራቅ እዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አሰፋ ቸኮል “ጦርነት ሁሉንም ፍጥረት የሚያወድም ሲኾን ሰላም ደግሞ ለሁሉም ፍጥረታት የሚያስፈልግ ልብስ ነው ብለዋል።
ታላቋን ሀገር ወደ ታላቅነቷ በፍጥነት መመለስ እንችላለን ነው ያሉት በንግግራቸው።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
