
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ ስብሰባ ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡
በንግግራቸውም፤ የኢትዮጵያ እና ህንድ ግንኙነት በርካታ ዓመታትን ማስቆጠሩን ጠቁመው፤ ታሪክና ባሕል የሚጋሩ ሀገራት መሆናቸውን አውስተዋል።
ህንድ በቀጣይ ለኢትዮጵያ የልማት ጉዞ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።
በተለይም በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሳይበር ሴኩሪቲ፣ በዐቅም ግንባታ፣ በግብርና፣ በትምህርት እና በጤና ዘርፎች በትብብር ለመሥራት ሀገራቸው ፍላጎት እንዳላት መናገራቸውን ኢዜአ አስነብቧል።
በቀጣናዊ ሰላምና ጸጥታ ዘርፍም የሕንድና ኢትዮጵያ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም መሠረት በይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
ከዓድዋ ድል ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያውያን ቅኝ ላለመገዛት በልበ ሙሉነትና በአንድነት ያደረጉት ተጋድሎና ያገኙትን ድል አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ አሁንም በቀጣናው ያላትን የሰላምና መረጋጋት ሚና ጠቅላይ ሚኒስትሩ አድንቀዋል።
በዓለም መድረኮችም ሕንድና ኢትዮጵያ ያላቸውን ድምፅ በማስተባበር ለታዳጊ ሀገራት መብት መከበር በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
