የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ።

2
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉን ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ በመሠረታዊነት ለመቀየር በለውጥ ሂደት ውስጥ እያለፈ ይገኛል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉን ፍርድ ቤት እንዲሁም የፍትሕ ሥርዓቱን ጠንካራ እና የኅብረተሰቡን አመኔታ ያረጋገጠ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ነው።
ይህንንም ለማጠናከር ይረዳ ዘንድ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር እየሠራ ይገኛል፡፡
በዛሬው ዕለትም የክልሉን የዳኝነት እና የፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል በጋራ መሥራት በሚችሉባቸው መስኮች ላይ በወርልድ ቪዥን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስ ካርመን ታርጆፍ ቲል እና ቡድናቸው ጋር ፍሬያማ ውይይት አካሂዷል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ተምሳሌት የኾነ ፍርድ ቤትን የመገንባት ርዕዩን በመግለጽ ለዚህም የክልሉን ፍርድ ቤቶች ተደራሽነት ለማረጋገጥ ከአካላዊ ተደራሽነት ጎን ለጎን በቴክኖሎጂ ተደራሽ በመኾን ክልሉን የዘመናዊ ዳኝነት መስጫ ማዕከል ለማድረግ እየሠራ መኾኑ በዕለቱ ተገልጿል።
አማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓቶችን ማጠናከር ለኢኮኖሚ እድገት እና ዘላቂ ሰላም ግንባታ ያለውን ሚና በተለይም የባሕላዊ ፍርድ ቤቶችን እውቅና አሰጣጥ እና አደረጃጀት እንዲሁም በእነዚህ ተቋማት ላይ የሚሠራ የአቅም ግንባታ ሥራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶት እየተተገበረ መሆኑ ተነስቷል።
የፍትሕ ተደራሽነት የሚገለጽበት ሌላው ዘርፍ የሕግ አገልግሎትን በተመለከተ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የተከላካይ ጠበቃ ጽሕፈት ቤትን ከማጠናከር አንጻር የተሠሩ ሥራዎችን እና የታቀዱ ተግባራትን በተመለከተም መክረዋል።
ለሕጻናት፣ ሴቶች እና ሌሎች ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ለማጠናከር፣ ለተጀመሩ የለውጥ እና የአሠራር ማሻሻያዎች የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት በሰው ኃይል አቅም ግንባታ ዘላቂነት እንዲኖረው ትኩረት መሰጠቱም ተገልጿል።
የተጀመረውን ሁሉአቀፍ የለውጥ እና የማሻሻያ ሥራ አስመልክቶ የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የሉካን ቡድን ጋር ውጤታማ የኾነ ውይይት ተካሂዷል፡፡
የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስ ካርመን በጠቅላይ ፍርድ ቤት ተገኝተው በመወያየታቸው እና ጉብኝት በማድረጋቸው ደስተኛ መኾናቸውን እና ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በአጭር ጊዜ ያስመዘገበው ለውጥ የሚደነቅ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
የአንድን ሀገር ሥርዓት ጠንካራ እና ውጤታማ ለማድረግ የዳኝነት ተቋሙ ጠንካራ መኾን መሠረታዊ መኾኑን የገለጹት ዳይሬክተሯ ድርጅታቸው ትኩረት በሚያረድግባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋር በጋራ ለመሥራት ደስተኛ እንደኾኑ ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አለምአንተ አግደው በበኩላቸው ሚስ ካርመን ባላቸው የተጨናነቀ የሥራ መርሐ ግብር ውስጥ ኾነው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን በመጎብኘታቸው አመስግነዋል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውጤታማ የኾነ የዳኝነት ሥርዓት ለመገንባት ርዕይ ሰንቆ እየሠራ ያለውን መሠረታዊ ለውጥ ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በመደገፍ በክልሉ የዳኝነት እና የፍትሕ ሥርዓት ላይ አሻራውን እንዲያሳርፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየእንቅስቃሴ ውስንነት በሚገድበው የሸማ ሥራ ለሌሎች ሰዎች ሥራ መፍጠር የቻለው ሥራ ፈጣሪ
Next article“የሰላም ትሩፋትን ለማግኘት ስክነት እና መወያየት ያስፈልጋል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)