
ከሚሴ: ታኅሣሥ 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ ከተማ አሥተዳደር ከተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ሕዝባዊ የሰላም አና የልማት ኮንፈረንስ ተካሂዷል።
በመድረኩ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደጀኔ ልመንህ፣ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ፣ የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኤልያስ አበበን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኀላፊዎች እና የከተማው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ የአጣዬ ከተማ ነዋሪዎች በከተማዋ ከዚህ በፊት በርካታ የሰላም መደፍረስ ያጋጥም እንደነበር ገልጸው በተሠራው የተቀናጀ የሰላም ሥራ አሁን ላይ ከተማዋ ፍፁም ሰላማዊ መኾኗን ተናግረዋል።
ከተማው ሰላም እንዲኾን ከሃይማኖት መሪዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመኾን ለሰላማችን ከመንግሥት ጋር እየሠራን ነውም ብለዋል።
ከአጎራባች የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሕዝቦች ጋር ያለን ግንኙነትም ጠንካራ በመኾኑ በጋራ እየተገበያየን እና እየኖርን ነው ብለዋል።
የአጣዬ ተደጋጋሚ ጉዳት የደረሰባት በመኾኑ በቀጣይ መንግሥት ከተማዋን መልሶ ለመገንባት እየሠራ ያለውን ተግባር አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኤልያስ አበበ የአጣዬ እና አካባቢው ሕዝብ ከመንግሥት ጋር በመኾን ሰላሙን አስጠብቆ ያለ ሕዝብ ነው ብለዋል።
ከአጎራባች ወንድም ሕዝቦች ጋር የተጀመረው የሰላም እና የልማት ተግባራትን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ አጣዬ የአብሮነት እና የሰላም ከተማ መኾኗን ገልጸዋል። በቀጣይም ሕዝቡ አብሮነቱን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት።
ከወንድም አጎራባች ሕዝቦች ጋር በጋራ እርሻዎችን በጋራ የማልማት እና በጋራ የመገበያየት ተግባርን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
የአጣዬ ከተማን እና የኤፍራታ ግድም ወረዳን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ የዞኑ መንግሥት በትኩረት እየሠራ መኾኑንም አስረድተዋል።
የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደጀኔ ልመንህ በአጣዬ እና አካባቢው የተገኘው ሰላም እንዳይቀለበስ ሕዝቡ ከመንግሥት ጋር ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል።
መንግሥት አሁንም ለሰላም የከፈተው በር ክፍት በመኾኑ የሃይማኖት መሪዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላትን ጥሪ በማድረግ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) አጣዬ የአብሮነት እና የሰላም ከተማ መኾኗን አረጋግጠናል ብለዋል።
የአጣዬ ሕዝብ የሰላምን ዋጋ የሚያውቅ በመኾኑ እና ታታሪ የሃይማኖት መሪዎች በመኖሩ የሰላም ከተማ መኾኗን አስረድተዋል።
የተገኘው ሰላም ዘላቂ እንዲኾን ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡ ኹሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
በቀጣይ አጣዬን እና አካባቢዋን ለመገንባት መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት በቅንጅት ሊሠሩ ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
