“ዘመናዊ ግብርናን ካላረጋገጥን የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ አንችልም” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

12
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎጃም ዞን የዘመናዊ ግብርና አውደ ርዕይ እና የግብርና ቴክኖሎጂ ርክክብ ሥነ ሥርዓትን አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ለግብርና ትልቅ ጸጋ ያለው አካባቢ ነው። ዞኑ ትርፍ አምራች እና ለዘመናዊ ግብርና የተመቸም ነው። በዞኑ 195 ትራክተሮች እና 30 ኮምባይነሮች መኖራቸውም በዕለቱ ተገልጿል።
የዳሞት ዩኒየን የቦርድ ሰብሳቢ ዘሪሁን ገላው በዩኒየኑ አማካኝነት የሜካናይዜሽንን ሥራ እየተገበሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂ ጊዜን የሚቆጥብ፣ ብክነትን የሚቀንስ እና ምርታማነትን የሚጨምር ነው ብለዋል። ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የመጠቀም ልምድ እንዳላቸው እና በኩታገጠም እያረሱ መኾናቸውን አንስተዋል። አርሶ አደሮች ጥቅሙን እየተረዱ ቴክኖሎጂን እየተጠቀሙ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ከወንበራማ ወረዳ ዳፍኔ ሻንብላ የኅብረት ሥራ ማኅበር የመጡት አዝመራው ልመነው ቴክኖሎጂን በአግባቡ እየተጠቀምን ነው፤ ነገር ግን በቂ ቴክኖሎጂ እየቀረበ አይደለም ነው ያሉት። መንግሥት ችግሮችን እንዲፈታም ጠይያዋል።
ቴክኖሎጂ ጉልበታችን እና ጊዜያችንን በመቆጠብ ምርታማነትን እየጨመረ ነው ብለዋል። ከዚህ በላይ የቴክኖሎጂ ግብዓት ከጨመረ ምርት እና ማርታማነት እየጨመረ ይሄዳል ነው ያሉት የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ ዘመናዊ ግብርና ቅልጥፍናን፣ ምርታምነትን እና ዘላቂነትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ተናግረዋል። የአርሶ አደሮችን ድካም እና ብክነትን በመቀነስ ምርታማነትን እንደሚጨምር ገልጸዋል።
ግብርናው ለሀገራዊ እድገት ወሳኝ ሚና እንዲኖረው ግብርናውን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መደገፍ እንደሚገባ አመላክተዋል። የግብርናው ዘርፍ ባለመዘመኑ በሚፈለገው ልክ ምርታማነት ሳይጨምር መቆየቱን ገልጸዋል።
ዘመናዊ ግብርና በቅድመ እና ድህረ ምርት ብልክነትን በመቀነስ ግብርናው በተፈለገው ልክ እንዲያድግ ያደርጋል ነው ያሉት። የሰውን እና የእንስሳት ኃይልን በቴክኖሎጂ በመተካት የተሳለጠ የግብርና ምርታማነት እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን ለዘመናዊ ግብርና ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል። የዞኑ አርሶ አደሮችም ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ፍላጎት እና ግንዛቤ ማደጉን ገልጸዋል። ምዕራብ ጎጃም ዞን ለሜካናይዜሽን የተመቸ ነው፣ በተመቸው ሥፍራ ሜካናይዜሽንን ለማሳደግ እየተሠራ ነው፣ ጥሩ ጅማሮም አለ ነው ያሉት። በሬን በትራክተር የመተካቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አንስተዋል።
ካለው ፍላጎት አንጻር ግን በቂ ቴክኖሎጂ ማቅረብ እንዳልተቻለ ነው የተናገሩት። ዘመናዊ ግብርን ለማረጋገጥ የፋይናንስ እጥረት እና ሌሎች ችግሮች እንዳሉም አመላክተዋል።
መሪዎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ለማረጋገጥ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል።
የአርሶ አደሮችን ምርታማነት ለማሳደግ፣ የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ እና ግብርናው እንደ ሀገር ላቅ ያለ ሚና እንዲኖረው ለማድረግ ዘመናዊ ግብርናን መተግበር ይገባል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ዘመናዊ ግብርናን ለማረጋገጥ እሳቤ ላይ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። የነበረው እና የቆዬው እሳቤ በሬ እና ገበሬ ነበር ነው ያሉት። በዚህም እርሻችን ሳይዘምን ቆይቷል ብለዋል።
ዘመናዊ ግብርናን ለማረጋገጥ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል። ለዘመናዊ ግብርና በተመቸው የአማራ ክልል በቂ ቴክኖሎጂ እንደሌለ እና በቴክኖሎጂ መታረስ ከሚገባው መሬት እየታረሰ ያለው ጥቂቱ ብቻ መኾኑን አመላክተዋል።
“ዘመናዊ ግብርናን ካላረጋገጥን የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ አንችልም ነው” ያሉት። በልቶ ከማደር ባለፈ ለገበያ የሚቀርብ ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር ዘመናዊ ግብርናን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ግብርናውን ማዘመን ለኢንዱስትሪ ግብዓቶችን መጨመር እና የኢንዱስትሪ ትስስርን መፍጠር ነው ብለዋል። ለኢንዱስትሪ በቂ ግብዓት ሲፈጠር የሥራ ዕድል ይፈጠራል፣ ምርት እና ምርታማነት ይጨምራል ነው ያሉት።
ዘመናዊ ግብርናን ለማረጋገጥ የቆዬውን አመለካከት መቀየር እና ኋላቀር አስተራረስን ማሻሻል ያስፈልጋል ብለዋል። የአማራ ክልል ዘመናዊ ግብርናን ለማሳካት እና የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል። የክልሉ ኢኮኖሚ የተመሠረተው በግብርና ነው፤ ግብርናውን በትኩረት መምራት የክልሉን የሰው ኃይል እና ኢኮኖሚን በአግባቡ መምራት ነው ብለዋል።
የጎጃም ሜዳዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማረስ እና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል። የአርሶ አደሮችን የተበጣጠሰ የአሥተራረስ ዘዴ ማሻሻል፣ በኩታ ገጠም እንዲያርሱ ማድረግ፣ የግብዓት አቅርቦትን በወቅቱ እና በበቂ ማቅረብ እንደሚገባም አንስተዋል።
በ25 ዓመታቱ የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት እቅድ ግብርናውን ዘመናዊ ለማድረግ ልዩ ትኩረት እንደተሠጠው አመላክተዋል። የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ቴክኖሎጂን በስፋት እና በጥራት ማቅረብ እንደሚገባም አመላክተዋል።
የቴክኖሎጂ ፍላጎቶችን በመለየት ለማሟላት የአማራ ኢንዱስትሪ እና ማሽን ቴክኖሎጂ እንዲያመርት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የፋይናንስ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ከባንኮች ጋር እየተሠራ መኾኑን አመላክተዋል።
አማራ ክልል በቂ የግብርና ቴክኖሎጂ እንዲኖረው እና በአቅሙ ልክ እንዲለማ በቁጭት መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል። አሁን ያለው የግብርና ቴክኖሎጂ ለክልሉ እንደማይመጥንም አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር 142 ሺህ የማኅበረሰብ ክፍሎች የጤና መድኅን ሕክምና ተጠቃሚ ኾነዋል።
Next article”አጣዬ የአብሮነት እና የሰላም ከተማ መኾኗን አረጋግጠናል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)