
ደብረ ብርሃን: ታኅሣሥ 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን የ2017 ዓ.ም የአፈፃፀም ግምገማ፣ እና የ2018 ዓ.ም እቅድ ኦረንቴሽን የንቅናቄ መድረክ የክልል እና የዞን መሪዎች እና የማኅበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት ተከናውኗል።
የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በ2017 ዓ.ም 92 በመቶ የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አፈፃፀም እንደ ከተማ መመዝገቡን ገልጸዋል።
በ2018 ዓ.ም የመድኃኒት አቅርቦት እና የጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል ከአምናው የላቀ አፈፃፀምን ለማስመስገብ በቅንጅት እና በቁርጠኝነት ይሠራል ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን የመረዳዳት እና የመተሣሠብ ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችን የሚገለጥበት ተግባር ነው ብለዋል።
ማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ በኋላ የዜጎች የመታከም ልምድ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
በክልል ደረጃ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ክፍያ መክፈል ለማይችሉ 23 በመቶ ለሚኾኑ የክልሉ ነዋሪዎች የነፃ ሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ማድረግ ተችሏልም ነው ያሉት።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ያለው አፈፃፀም በ2018 ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ ኀላፊ በቀለ ገብሬ በበኩላቸው በከተማ አሥተዳደሩ በ2017 ዓ.ም ከ30 ሺህ በላይ እማወራዎች እና አባወራዎች የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አባል ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በቤተሰብ አባላት ደረጃ 129 ሺህ ነዋሪዎች ታቅፈዋል ብለዋል። 142 ሺህ ነዋሪዎች በተመላላሽ እና ተኝቶ ሕክምና የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አቶ በቀለ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ:- ሥነ ጊዮርጊስ ከበደ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
