ገዳ ባንክ በበጀት ዓመቱ 342 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ አገኘ።

9
አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ገዳ ባንክ በበጀት ዓመቱ 342 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታውቋል።
ባንኩ የባለአክሲዮኖች 4ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዷል።
የገዳ ባንክ ቦርድ ሰብሳቢ ሐሰን ሁሴን በ2024/25 በጀት ዓመት በሃብት ማሰባሰብ እና ትርፋማነት ባንኩ ስኬት አስመዝግቧል ብለዋል። ወጭን የመቆጣጠር አወንታዊ ባሕሉን በማሳደግ በአስቸጋሪ ጊዜ ውስጥም ኾኖ ትርፋማነቱ ማደጉን ገልጸዋል።
ባንኩ በበጀት ዓመቱ ከታክስ በፊት 448 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን የገለጹት የቦርዱ ሰብሳቢው አጠቃላይ የተጣራ ትርፉም 342 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ደርሷል ነው ያሉት። በዚህም የአንድ አክሲዮን የተጣራ የትርፍ ክፍፍል ዋጋ 132 ነጥብ 4 ብር ኾኗል ብለዋል።
የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ 7 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የደረሰ ሲኾን አጠቃላይ የደንበኞቹ ብዛት ከ575 ሺህ በላይ መሻገሩንም ተናግረዋል። ገዳ ባንክ በበጀት ዓመቱ የከፈታቸውን አዳዲስ 15 ቅርንጫፎችን ጨምሮ አጠቃላይ ብዛታቸው 100 መድረሱንም ነው የባንኩ ቦርድ ሰብሳቢ የገለጹት።
የባንኩ አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መድረሱ የተገለጸ ሲኾን የተፈረመ ካፒታሉ ደግሞ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ደርሷል።
የባንኩ አጠቃላይ ሃብትም ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ተናግረዋል።
ባንኩ እራሱን በማዘመን የተቀላጠፈ አገልግሎትን ለደንበኞቹ ለመስጠት የሚያስችል ቴክኖሎጂን በማልማት የዲጂታል ዘርፉ ላይ በትኩረት እየሠራ መኾኑንም የቦርዱ ሰብሳቢው ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሔም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleስልጠናው በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን መለየት የሚያስችል አቅም የፈጠረ መኾኑን ሰልጣኞች ተናገሩ።
Next articleደብረ ብርሃን ከተማ የኢንቨስትመንት ፍሰትን በአግባቡ በመጠቀም ለውጥን መሬት ላይ በማሳየት ተምሳሌት ናት።