“ሰው አክባሪ ለኾነው የጎንደር ከተማ ሕዝብ ታላቅ ክብር አለኝ” ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል

14
ጎንደር: ታኅሣሥ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ” የጉባ ብስራቶች፣ የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች” በሚል መሪ መልዕክት ውይይት እየተካሄደ ነው።
በውይይቱ የፌዴራል፣ የክልል እና የከተማዋ የሥራ ኀላፊዎች በጋራ ነው ከጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ጋር እየመከሩ የሚገኙት።
ምክክሩ በዋናነት በከተማዋም ይሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተሠሩ ያሉ ትሩፋቶችን ለማስቀጠል ያለመ ነው።
በመርሐ ግብሩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው የአብሮነት ተምሳሌት እና የሥልጣኔ ባለቤት የኾነችው ጎንደር ከተማ ትኩረት ተነፍጓት ቆይቷል ብለዋል።፣ በጸጋዋ ልክ እንዳትለማ ተደርጋ እንደነበርም አንስትዋል።
አሁን ላይ በከተማዋ በርካታ ስኬታማ የልማት ሥራዎች እየተከናዎኑ እንደሚገኙም አቶ ቻላቸው ገልጸዋል።
በውይይት መድረኩ የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) በሀገር አቀፍ ደረጃ መንግሥት በግብርና ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል በዚህም ዘርፈ ብዙ ተግባራት ሠርተናል ብለዋል።
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል በዚህ ፈታኝ ሰዓት የከተማዋን እድገት ከፍ ለማድረግ እና የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተጉ ለሚገኙ የሥራ ኀላፊዎች እንዲሁም “ሰው አክባሪ ለኾነው የጎንደር ከተማ ሕዝብ ታላቅ ክብር አለኝ” ብለዋል።
በጎንደር ከተማ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው መመልከታቸውን የገለጹት ሚኒስትሯ ያጋጠመውን የሰላም እጦት በመቋቋም በገጠርም ይሁን በከተማ ዘርፍ የተሟላ ልማት እየተከናወነ መኾኑን መታዘባቸውን ነው የተናገሩት።
እየተከናወኑ የሚገኙ የባሕል እና የልማት ሥራዎች የሀገር ባሕል እና ወግ ያማከሉ፣ የሕዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ መኾን እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በየደረጃው ከሕዝብ ጋር የሚደረጉ ውይይቶች የሕዝብን ጥቅም የሚያረጋግጡ እና ሕዝብ የሚያነሳቸውን ችግሮች የሚፈቱ መኾን እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
ኀላፊነት የተሰጣቸው አካላትም ሕዝብ የሚያነሳቸውን ችግሮች ትኩረት ሰጥቶ የመሥራት ብቃታቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።
ዘጋቢ:- ተስፈየ ጋሹ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ከሰላም ትሩፋት መጠቀም ሲገባን የግጭት ገፈት ቀማሽ ኾነን ቆይተናል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next articleማኅበረሰቡን ያላቀፈ የወንጀል መከላከል ተግባር ውጤታማ ሊኾን አይችልም።