“ከሰላም ትሩፋት መጠቀም ሲገባን የግጭት ገፈት ቀማሽ ኾነን ቆይተናል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

12
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከፍኖተ ሰላም፣ ከጅጋ ከተማ እና ከጃቢ ጠህናን ወረዳ ነዋሪዎች ጋር በፍኖተ ሰላም ከተማ እየተወያዩ ነው።
በውይይቱ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዕዝ አዛዥ ሌትናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ ዕድሜዓለም አንተነህ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በርካታ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኃይል ባደረጉት ተጋድሎ አሁን ላይ ጽንፈኛው ቡድን ተመትቷል፤ ተበትኗል ነው ያሉት።
የጸጥታ ኃይሉ የመፈጸም አቅም እያደገ መኾኑንም ተናግረዋል። ሕዝቡም ጽንፈኛውን አምርሮ ጠልቷል ነው ያሉት። ነገር ግን አሁንም ሙሉ ለሙሉ ሰላም አለመረጋገጡን እና ጽንፈኛውም በሕዝብ ላይ ጉዳት እያደደረሰ መኾኑን ተናግረዋል። ጽንፈኛው ቡድን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የሚፈጽም፣ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ያራቀ፣ ማኅበራዊ ሕይዎትን ያስተጓጎለ መኾኑንም ገልጸዋል።
አሁንም የጽንፈኛው ሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳ የጠለፈው የማኅበረሰብ ክፍል መኖሩን እና ጽንፈኛውን በተገቢው መንገድ ያለመታገል ችግር እንዳለ ተናግረዋል። እውነት ላይ ቆሞ መምከር እና ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ከዚህ በላይ ሕዝብ በችግር ውስጥ እንዲኖር መፍቀድ እንደማይገባም ተናግረዋል።
አሁን ለተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም ላበቃው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኃይል ምስጋና አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ባለፉት ዓመታት የተፈጠረው ችግር ከአማራ ሕዝብ ባሕል እና እሴት ያፈነገጠ፣ የከፋ ጉዳት ያደረሰ እንደኾነም ተናግረዋል። የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሕዝብን መጉዳቱንም ገልጸዋል።
ችግሩን ከሥረ መሠረት የሚመረምር እና መፍትሄውን የሚያመላክት የሃይማኖት አባት እና የሀገር ሽማግሌ ከሌለ ሕዝብ ይጎዳል ብለዋል። ባለፉት ዓመታት የስክነት እና የአስተውሎት ችግሮች እንደነበሩ ተናግረዋል። ባለፉት ዓመታት የተፈጠረው ችግር ለነገ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድርም ገልጸዋል።
ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ መምከር እና መደማመጥ እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል። የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የእሴት እና የባሕል መሸርሸር ፈጥሯል ነው ያሉት። የሰው ሕይዎት ተቀጥፏል፤ ንጹሐን በግፍ ተገድለዋል፤ መካካድ ነበር ነው ያሉት።
ትውልድ ባልተገራ ቦይ እንዲፈስ የሚያደርግ ችግር መፈጠሩንም ተናግረዋል። የሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶች ተቃልለዋል፤ ለእርቅ የሄዱ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ተንገላተዋል፤ ተገድለዋል ነው ያሉት። በክልሉ ከፍተኛ የኾነ የመሠረተ ልማት ጉዳት እንደደረሰም ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቶች ወድመዋል፤ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል፤ የጤና ተቋማት ተዘርፈዋል ነው ያሉት። የሰው፣ የምርት እና የአግልግሎት እንቅስቃሴ መገታቱንም ተናግረዋል። በትምህርት ላይ የሚደረግ ጥቃት እና ደባ፣ የማኅበረሰብን የነገ ጉዞ የሚያጨልም ነው ብለዋል።
የክልሉ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ችግር እንደገጠመውም ገልጸዋል። የክልሉ ውስጣዊ አንድነት እንዲሸረሸር ማድረጉንም አንስተዋል። የባዕዳንን ተልዕኮ የሚያስፈጽም ግጭት መኾኑን ተናግረዋል። የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሕዝብን በሥነ ልቦና ጫና እንዲጎዳ አድርጓል ነው ያሉት።
ባለፉት ዓመታት ከሰላም ትሩፋት መጠቀም ሲገባን የግጭት ገፈት ቀማሽ ኾነን ቆይተናል ብለዋል። ከዚህ ችግር ውስጥ ለመውጣት እውነተኛ ውይይት እና ምክክር ያስፈልጋል ነው ያሉት።
አሁን ካለው አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም መሸጋገር እንደሚገባም ተናግረዋል። ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ለምለሙን ምድር ለልማት እና ለምርት ማዋል እንደሚገባ ገልጸዋል። ለነገ ታላቅ አበርክቶ እንዲኖረን ዛሬ ላይ የድርሻችን መወጣት አለብን ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየፖሊዮ በሽታን ለመከላከል እየተሠራ ባለው ተግባር ማኅበረሰቡ አጋዥ መኾን አለበት።
Next article“ሰው አክባሪ ለኾነው የጎንደር ከተማ ሕዝብ ታላቅ ክብር አለኝ” ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል