ሕጻናት ክትባት ማግኘት መብታቸው ነው።

7
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከታኅሣሥ 3 እስከ 6/2018 ዓ.ም ድረስ የሚካሄደውን የልጅነት ልምሻ (ፖልዮ) የአራተኛ ዙር ክትባት ዘመቻ ሥራ ጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የተገኙት የባሕር ዳር ወረዳ ሀገረ ስብከት ሥራ አሥኪያጅ ቄስ መልአከ ሰላም ለዓለም ጌታሁን በኢትዮጵያ በርካታ በሽታ ተከስተው ነበር፤ ከነዚህም መካከል አንዱ የልጅነት ልምሻ ነው ብለዋል።
በመላው ዓለም በጊዜው ብዙ ሰዎች አንገታቸውን የደፉበት፣ የተሰቃዩበት እንዲሁም በርካታ ልጆችን ያሳጣ ነበር ነው ያሉት።
አሁን ግን የልጅነት ልምሻ ክትባት በሁሉም ሰው በር ድረስ መጥቶለታል፤ ይህን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ልጆቹን እንዲያስከትብ ጥሪቸውን አስተላልፈዋል።
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ ሙሐመድ ኢብራሂም በበኩላቸው ሕፃናት ላይ መሥራት ትውልድ ላይ መሥራት ነው ብለዋል።
ሕፃናት ጤነኛ ኾነው ለቤተሰብም ለሀገርም የሚጠቅሙ እንዲኾኑ ኅብረተሰቡ ልጆቹን በማስከተብ ትውልድን እንዲታደጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ፖሊዮን ከሀገር ብሎም ከዓለም ለማጥፋት ጥረት እየተደረገ መኾኑን አንስተዋል። የአሁኑ ዘመቻም የዚሁ አካል መኾኑን ገለጸዋል።
ከዚህ በፊት ክትባቱ ይሰጥ የነበረው እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለኾኑ ሕጻናት እንደነበርም ዋና ዳይሬክተሩ አንስተዋል። አሁን ግን የበሽታው ምልክት ከአምስት ዓመት በላይ በኾኑ ሕጻናት ላይ መታየት ስለጀመረ ከአምስት ዓመት በላይ ላሉትም ክትባቱን መስጠት ስለማስፈልጉ ጠቅሰዋል።
ክትባቱ በ 14 ዞኖች እና ከተማ አሥተዳደሮች እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለኾኑት ሕጻናት ይሰጣል ብለዋል።
በተጨማሪም በስምንት ዞኖች እና ከተማ አሥተዳደሮች ደግሞ እድሜያቸው እስከ አሥር ዓመት በታች ለኾኑ ሕጻናት ይሰጣል ነው ያሉት።
በአጠቃላይ ከ5 ሚሊየን በላይ ሕጻናት ክትባቱን ያገኛሉ ያሉት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ የፖሊዮ ክትባቱ ቤት ለቤት፣ በትምህርት ቤቶች እና በመጠለያ ጣቢያዎች እየተሰጠ ነው ብለዋል።
ለዘመቻ መሳካት ሁሉም ባለድርሻ አካላት እና ኅብረተሰቡ በባለቤትነት ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አድርገዋል።
ሁሉም ሕጻናት ክትባት የማግኘት መብት አላቸው። ልጆቹን በማስከተብ በጤንነት እንዲያድጉ ኅላፊነታችንን እንወጣ ብለዋል።
ዘጋቢ:- ሰመሀል ፍስሀ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleመሪዎች በየአካባቢው ያሉ እምቅ ሃብቶችን ለይተው ሊያለሙ ይገባል።
Next article65 ታጣቂዎች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀበሉ።