ግጭት ሕዝብን ያሰቃያል።

23
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በምዕራብ ጎጃም ዞን ከቋሪት ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ሰላምን ለማረጋገጥ ጥረት ስናደርግ ኖረናል፤ ነገር ግን ሰሚ አጥተን ነው የቆየነው ብለዋል። ጦርነት አንፈልግም፤ እኛ የምንፈልገው ልማት ነው፤ ግጭት ሕይዎትን ከመቅጠፍ የዘለለ ጥቅም የለውም ነው ያሉት።
ከጠንካራ ሽፍታ ደካማ መንግሥት ይሻላል ያሉት ነዋሪዎቹ ግጭት ሕዝብን እየጎዳ ነው፤ መንግሥት እንዲጠናከር እና ሰላምን እንዲያስከብር እንፈልጋለን ብለዋል። ሀገር ያለ መንግሥት ምንም ናት፤ በመንግሥት በኩል ችግር ሲኖር እንኳን ቁጭ ብሎ ተወያይቶ መፍታት ይሻላል እንጂ ግጭት አይጠቀምም ነው ያሉት።
በሆይ ሆይታ የተጀመረው ግጭት ሕዝብን ለከፋ ጉዳት እንደዳረገም ተናግረዋል። ተተኪ ልጆቻችን ያለ በደላቸው ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል፤ ነገ ተስፋ የምናደርግባቸው ልጆች እንዳይኖሩን ኾነናል ነው ያሉት።
በጸጥታ ችግር ምክንያት ተጀምረው የነበሩ የልማት ሥራዎች ተቋርጠዋል፤ ይህ ደግሞ ሕዝብን ለከፋ ጉዳት ዳርጓል፤ ጦርነት በቃን፣ በደል በዝቶብናል፤ አይዟችሁ ካላችሁን እኛ ሰላምን ለማረጋገጥ እንሠራለን ብለዋል።
እኛ የምንፈልገው ልጆቻችን እንዲማሩ እና ሠርተን እንድንለወጥ ነው። የጸጥታ ችግሩ በሰላም ገብቶ ለመውጣት አስቸግሯል፤ እናቶች ወደ ጤና ተቋማት እንዳይሄዱ ተደርገዋል፤ እንዲሞቱ ተፈርዶባቸዋል፤ አምቡላንስ እየተነጠቀ ለታጣቂ ማመላለሻ ኾኗል ብለዋል።
ከሁሉም አስቀድሞ ሰላምን እንደሚፈልጉም ተናግረዋል። በጫካ የሚገኙት ታጣቂዎች ሕዝብ እየተማረረ መኾኑን አውቀው ሰላም መፍጠር ይገባቸዋል ነው ያሉት። የያዙት መንገድ ሕዝብን እያሰቃየ መኾኑን መረዳት እንደሚገባቸውም አንስተዋል።
ግጭት ሕዝብን ያሰቃያል እንጂ የሚፈጥረው መልካም ነገር የለም ብለዋል። በዚህ ወቅት የሚያስፈልገው አንድነት እንጂ ግጭት እና መለያየት አይደለም ነው ያሉት። ሰላምን የሰበኩ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች እንግልት እና ማስፈራራት እየደረሰባቸው መኾኑን ተናግረዋል።
ተው ሰላም ይሁን ብለን ስንነጋገር እንኳን ምን ይደርስብን ይኾን እያልን በስጋት እየኖርን ነው፤ መገዳደል ይበቃል፣ ሰላም እንዲመጣ እንፈልጋለን ብለዋል። ሕዝብ ተዘርፎ ተዘርፎ ባዶውን ቀርቷል፤ ከዚህ በላይ መዘረፍ ይበቃል ነው ያሉት።
መንግሥት የጀመረውን የሰላም አማራጭ እናደንቃለን፤ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም እንፈልጋለን፤ የጦርነት መጨረሻው መወያየት ነው ብለዋል።
መንግሥት ሰላምን በማረጋገጥ የልማት ሥራዎችን እንዲሠራም ጠይቀዋል። የተጀመረው የመንገድ ፕሮጄክት በፍጥነት ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲኾንም አንስተዋል። ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች ሢሠሩ ሰላምም ይረጋገጣል ነው ያሉት። ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ የቋሪት አካባቢ ሕዝብ በጽንፈኛው ቡድን ከፍተኛ በደል ሲደርስበት መቆየቱን ተናግረዋል። በአንድነት ከቆማችሁ አካባቢያችሁን ሰላም ማድረግ ትችላላችሁ ነው ያሉት።
ከዚህ በላይ እየተሰቃያችሁ መኖር አይገባችሁም፤ ለሰላማችሁ በጋራ መሥራት ይጠበቅባችኋል ብለዋል። ጽንፈኛው ኃይል መንገድ ላይ እየዘረፈ እና እየቀማ ሕዝብን እያሰቃየ መኾኑንም ተናግረዋል። ጽንፈኛው ቡድን የመንግድ ፕሮጄክቶችን ጨምሮ ሌሎች የልማት ሥራዎች እንዲጓተቱ እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።
ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የሕዝብ የልማት ጥያቄዎች እንዲፈቱ እንደሚሠራም ተናግረዋል። ሰላምን ማረጋገጥ ከተቻለ መለወጥ የሚያስችል ሃብት እንዳለም ገልጸዋል። ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሠራም አመላክተዋል።
የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የጀመሩትን ሰላምን የማረጋገጥ ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየግብርና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት የክልሉ ግብርና ቢሮ በትኩረት እየሠራ ነው።
Next article“ከ5 ሚሊዮን በላይ ሕጻናትን የፖሊዮ ክትባት ለመስጠት ታቅዷል” የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት