“ብሔር እና እምነትን መሠረት ያደረገ የጽንፈኝነት አስተሳሰብ ለሕዝባችን አይበጅም” አቶ ይርጋ ሲሳይ

22
ደሴ: ታኅሣሥ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከደሴ ከተማ ወጣቶች ጋር ተወያይተዋል።
ወጣቶቹ በውይይታቸው ጽዱ እና ውብ ከተማ ያስፈልገናል ያሉ ሲኾን ደሴ ከተማ ላይ የወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ባለመኖሩ ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አንስተዋል።
የሰላም ጉዳይ የክልላችንን ሕዝብ እየጎዳው በመኾኑ ሕዝብን በማወያየት የመጨረሻ መፍትሔ እንዲሰጠውም ጠይቀዋል። ወጣቶች ሥራ ባለማግኘታቸው ወደ አልባሌ ቦታ እና ሱስ እየገቡ በመኾኑ ሥራ ፈላጊ ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት በሚደረገው ጥረት ያሉ አሠራሮች እንዲስተካከሉ የሚል ሃሳብም አንስተዋል።
ደሴ ከተማ ኢንዱስትሪ ያስፈልጋታል ያሉት ወጣቶቹ የዋጋ ንረትን መግታት እና የተጀመሩ ሥራዎችን ማጠናቀቅ እንደሚገባ አመላክተዋል። ወጣቱ ልማቱን ለማገዝ ዝግጁ መኾኑንም ተናግረዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ከወጣቶች የተነሱ ጥያቄዎችን በመለየት ተግባራቶች ይሠራሉ ብለዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ ሕዝብን አሳታፊ የሚያደርጉ ዘርፎችን በመለየት እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል። ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ከኃይል አቅርቦት ጋር የሚነሳውን ጥያቄ ለመፍታት በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በሥራ ዕድል ፈጠራ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ ያሉት አቶ ሳሙኤል፤ ይህን በማጠናከር ከወጣቱ ጋር ተቀራርበን እንሠራለን ነው ያሉት። ከሠራነው ይልቅ የምንሠራው ይበዛል እና ወጣቱ ሰላሙን በማስጠበቅ እና ልማቱን በማገዝ በቅርበት ሊያግዘን ይገባል ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሀ ደሳለኝ ወጣቶች አካባቢን መቀየር የሚያስችል ሀሳብ ያላችሁ በመኾኑ ሰላም እና ልማትን ለማምጣት በሚደረገው ጥረት በትብብር መሥራት አለባችሁ ብለዋል።
ጫካ የገባው ኃይል የሕዝብ ጥያቄን ሽፋን በማድረግ መከራ እያደረሰ በመኾኑ ወጣቶች ይህን አውቃችሁ ለሰላም እንድትሠሩ ሲሉም አደራ ብለዋል።
ወሎየነት ለአብሮነት ያለውን እሴት በማስቀጠል ለአንድነት መትጋት እንደሚገባም አመላክተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ በክልላችን ያለውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ወጣቶች ተሳትፏችሁን አጠናክሩ ብለዋል። ለክልሉ ሰላም የድርሻችሁን ልትወጡ ይገባል ነው ያሉት።
ከችግሮች ለመውጣት አቋማችን የጸና በመኾኑ ወጣቱ ከሚሰጠው የጥፋት አጀንዳ በመውጣት ከመንግሥት ጎን ኾኖ መታገል አለበት ብለዋል።
“ብሔርተኝነትን እና እምነትን መሠረት ያደረገ የጽንፈኝነት አስተሳሰብ ለሕዝባችን የማይጠቅም ነው” ያሉት አቶ ይርጋ በወሎየነት የአብሮነት እሴት መጽናት አለባችሁ ብለዋል።
በአካባቢው ያሉ መልካም ጸጋዎችን ለመጠቀም ሰላም ያስፈልጋል፤ ይህንን መደገፍ እና መተባበር ከወጣቶች እንደሚጠበቅም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ ተመስገን አሰፋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleምስራቅ ዕዝ በጎጃም ቀጣና የሚያደርገውን ሕግ የማስከበር ኦፕሬሽን አጠናክሮ መቀጠሉን አስታወቀ።
Next articleየአካባቢን ጸጋ በመለየት ማልማት ላይ መሪዎች ቀዳሚውን ሚና መወጣት አለባቸው።