
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው ዕዝ እንዳስታወቀው 200 ጽንፈኞችን ደምስሷል፤ 53 አቁስሏል፤ 41 ተማርከዋል፤ 19 እጃቸውን ሰጥተዋል፤ 37 ደግሞ በምኅረት ገብተዋል፡፡
ምስራቅ ዕዝ ከኅዳር 18 እስከ 30/2018 ዓ.ም ባደረገው የተቀናጀ ስምሪት፣ በባሕር ዳር፣ በሰሜን ጎጃም፣ በአዊ እና በምዕራብ ጎጃም ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ተሰግስጎ የሕዝብን ሰላም ሲያደፈርስ፣ ሲዘርፍ እና ሲያወድም የነበረውን ኀይል የገባበት ድረስ ገብቶ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ማድረሱን ገልጿል፡፡
ምስራቅ ዕዝ በቀጣናው ከሚገኘው ከአማራ ክልል የጸጥታ ኀይል ጋር በመጣመር በወሰደው ተከታታይ ርምጃ ጽንፈኛውን ተስፋ ያስቆረጡ ምቶችን አሳርፎበታል፡፡ በዚህም ሰላም አዋኪው ታጥቋቸው የነበሩ 174 ኤ ኬ ኤም/ክላሽ፣ 191 የቃታ ጠመንጃ፣ ስድስት ቺቺ፣ 14 ሽጉጥ፣ 15 ቦምብ እና 14 ሊፈነዱ የተዘጋጁ ፈንጂዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
በተለይም ጫት ዋርካ በተባለ ቦታ ላይ በተደረገ ኦፕሬሽን ጽንፈኛው ይመጣብኛል ብሎ ባልጠበቀው ቦታ ሠራዊቱ በሌሊት ተጉዞ ሞርተር ያለበትን ቦታ ከበባ በማድረግ 82 ሚሊ ሜትር ሞርተር እንደተጠመደ መማረክ ችሏል፡፡ ከሞርተሩ ጋር ሁለት ቅንቡላ ከነአባሪዎቹ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም 706 የተለያዩ ተተኳሾች፣ አንድ የጦር ሜዳ መነጽር፣ ስድስት የመገናኛ ሬዲዮ፣ ሦሥት ጀነሬተሮች፣ 130 ኩንታል ለቀለብ አከማችቶት የነበረ እህል ተይዟል፡፡
ጽንፈኛው ሲገለገልባቸው የነበሩ 66 ሞተር ሳይክሎች በወገን ከበባ ውስጥ መኾኑን ሲያውቅ አውድሟቸዋል፡፡
ኮሮቹ ባደረጉት የተጠና ስምሪት በአካባቢው ሕዝብን ሲበድሉ እና ሲያንገላቱ የነበሩ ዋና ዋና የጽንፈኛው አመራሮች ላይ እርምጃ መውሰዳቸው ተጠቁሟል።
ጽንፈኛው እና ዘራፊው ቡድን የደረሰበትን ምት መቋቋም ስላቃተው የታጠቀውን መሳሪያ በየጥሻው እየጣለ፣ እየተበታተነ እና እጅ እየሰጠ ይገኛል፡፡ ባለፉት 13 ቀናት ብቻ 56 ጽንፈኞች እጃቸውን ለመንግሥት ሰጥተዋል፡፡
ምስራቅ ዕዝ ባደረጋቸው የጸረ-ሽምቅ ኦፕሬሽኖች የባንዳዎችን ተልዕኮ እያከሸፈ፣ ወደ ሕዝብ ጥፋት የተሰነዘሩ እጆችን እያሳጠረ ይገኛል፡፡
በአንጻሩ የጽንፈኛው አመራሮች በጎረቤት ሀገር ድንበር ላይ ኾነው መሬት ላይ የሌላቸውን ታጣቂ እንዳላቸው በማስመሰል አሁንም የጥፋት ነጋሪት እየጎሰሙ ይገኛሉ፡፡ ሕዝባችን ይህንን መሰሪ ፕሮፖጋንዳ ወደ ጎን በመተው ሰላሙ ዘላቂ እንዲኾን ዘብ መቆም ይጠበቅበታል፡፡
ምስራቅ ዕዝ የጎጃምን ሰላም ለማረጋገጥ የተሰጠውን ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮ በብቃት እየተወጣ ይገኛል፡፡ የኅብረተሰቡን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ለሰላም ጠንቅ የኾኑ ዘራፊዎችን የገቡበት ገብቶ እያደነ ሕግ ማስከበሩን የሚቀጥልበት መኾኑን ዕዙ አስታውቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
