
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሥልጠና ላይ ያሉ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር እና የሰሜን ጎጃም ዞን መሪዎች በባሕር ዳር ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ያገኘናቸው የደቡብ አቸፈር ወረዳ አመራር ሙሉቀን ክንዴ ከሥልጠናው በኋላ በመንግሥት የሚሰጠውን ተልዕኮ ተቀብሎ ለመሥራት ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ሰላሙን በማስፈን እና ልማትን በማጠናከር ኢንዱስትሪን የምናስፋፋበት ኹኔታ ይፈጠራልም ብለዋል። የደቡብ ሜጫ ወረዳው አመራር ዘውዱ እንዳለው በበኩላቸው በብልጽግና መንግሥት ኢንዱስትሪ እየተበረታታ መኾኑን በሥልጠናው እና በጉብኝታችን አረጋግጠናል ብለዋል።
ልማትን ለማስቀጠል ሰላምን በማስፈን ወጣቶችም ከኢንዱስትሪው ዘርፍ የሥራ እድል እንዲያገኙ ሰላማችንን ማረጋገጥ እንዳለብን ተረድቻለሁ ነው ያሉት።
ሌላኛዋ የሰሜን ጎጃም ሠልጣኝ አንቺንአሉ አረጋ በሥልጠናው እና በጉብኝቱ ያየነው የልማት እቅዳችን ማሳካት እንደምንችል አሳይቶናል ብለዋል።
የተጎበኙት የኢንዱስትሪ መንደሮችም የልማት ጥያቄዎችን የሚመልሱ እንደኾኑ አንስተዋል። የየደረጃው መሪ ባገኘው ሥልጠና ተጠቅሞ ከኅብረተሰቡ ጋር ኾኖ ሰላሙን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል። በተሳሳተ መንገድ ታጥቀው የወጡ ወንድሞቻችንም ተመልሰው ልማትን በጋራ ማሳለጥ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምን ጨምሮ ሌሎቹም ፕሮጀክቶች ለወጣቶች ለሥራ እድል ፈጠራ፣ ለጤና እና ለሥነ ምግባር ግንባታ ያግዛል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ብርሃን ንጉሤ በከተማቸው ከ13 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን ጠቅሰው የሥራ እድል በመፍጠር እና የውጪ ምንዛሪ በማስገኘት የሀገር ምጣኔ ሃብትን እንደሚያሳድጉ ገልጸዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪዎቹ በጥሩ የሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደሚገኙም ተናግረዋል። በአራት ዘርፎች 268 ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል።
ኢንዱስትሪዎች ሰፊ ግብዓት ስለሚፈልጉ በተለይ ግብርናው ሰፊ ግብዓት ማቅረብ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል። ለዚህም ትስስር እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።
ኢንቨስትመንት ሰላም ስለሚፈልግ የከተማችን ሰላም ምቹ ነው፤ በሌላው አካባቢም ሕዝብ እና መሪው ለሰላም በትኩረት መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።
ባሕር ዳር ሰላም ናት ያሉት ኀላፊዋ ልማቷን በኮሪደር ልማት እና በኢንዱስትሪ ለማሳደግ እየተሠራ ነው። ባለሃብቶችንም እየተቀበልን ነው ኑ አብረን እናልማ ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
