ቀይ ባሕርን በተመለከተ የታሪክ እዳው ከኋላችን ቢኾንም የታሪክ አደራችን ግን ከፊታችን ነው።

118

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አንድነት ከድሮም መገለጫዋ የኾነችው ኢትዮጵያ በልጆቿ የተባበረ ክንድ ለብዙዎች ሕልም የሚመስለውን የሕዳሴ ግድብ እውን ካደረገች ወራቶች ተቆጠሩ።

ዳሩ ግን ክስ እና ከእውነት የራቀ ውንጀላ መገለጫቸው የኾኑ ጥንተ ጠላቶች ዛሬም እንደ ትናንቱ የሀሰት ማመልከቻ ማስገባታቸውን አላቆሙም። በዚህ ፍሬ የሌለው ከንቱ ዲስኩር ደግሞ ግብጽ የፊታውራሪነቱን ቦታ እንደያዘች ናት።

ግብፅ ዛሬም እንደ ትናንቱ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረኾች የመክሰሷ ነገር መሠረታዊ ምክንያቷ ምን ይኾን?

የመኖሬ ምሥጢር የኾነው ዓባይ በመገደቡ ሕዝቦች ለዘርፈ ብዙ ርሃብ እና እልቂት ሊዳረጉ ነው ስትል የነበረው ክስ ሕዳሴ ግድብም እውን ሲኾን እንዴትስ አያቆምም? ዛሬም በየመድረኩ የመፈረጇ ምሥጢር ምን ሊኾን ይችላል?

የዓባይ ውኃ አጥኝው ስለአባት ማናዬ “የዓባይ ፖለቲካ እና የባዕዳን ተልዕኮ” በሚለው መጽሐፉ ላይ 85 በመቶ የዓባይ ውኃ ድርሻ ያላት ኢትዮጵያ ለግብጽ አፈር እና ውኃ ብቻ ሳይኾን ፍቅርንም ስትልክ ኖራለች ሲል በመጽሐፉ አትቷል።

በአንጻሩ ኢትዮጵያ ለግብጽ ለም አፈር እየላከች ራሷ ግን በተደጋጋሚ በርሃብ ስትጠቃ እንደኖረችም አስፍሯል። የዓባይ ወንዝ ከፍትሕ አፈንግጦ የግብፅን በረሃ እያረሰረሰ እና እያለማ መኖሩንም አትቷል።

ለባሕረ ሠላጤው ሀገራት በግብርና ምርቶች ብቻ ሳይኾን በኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ብዙ ገቢም ስታገኝ እንደኖረች በመጽሐፉ ላይ ጠቅሷል። ያ ሁሉ ሲኾን ታዲያ ግብጽ ለኢትዮጵያ የምትከፈላት የሀሰት ክስ እና ውንጀላ ነው ሲልም ያክላል። ይህ ትናንትም የነበረ ዛሬም ድረስ የቀጠለ ሀቅ ኾኖ ዘልቋል።

አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ የዓባይ ውኃ አጥኝ ከኾነው ጋዜጠኛ እና ደራሲ ስለአባት ማናዬ ጋር የግብጽ አሁናዊ ክስ በኢትዮጵያ ላይ ምን አንደምታ አለው ሲል ቆይታ አድርጓል።

የዓባይ እና የግብጽ የውኃ ፖለቲካ አታካራ ትናንትም የነበረ፣ ዛሬ ድረስ ያለ እና ወደፊትም የሚቀጥል ነው ብሏል። መፍትሔው ግን ታሪክ ቀያሪ እንደኾነው የሕዳሴ ግድብ አይነት ታሪኮችን በተግባር መድገም ነው ይላል።

የዓባይ ውኃ የጂኦ ፖለቲካዊ ኢ-ፍትሐዊነት ስሪት በዓለም ተወዳዳሪ የሌለው ነው ይላል ጋዜጠኛ፣ ደራሲ እና የውኃ አጥኝው ስለአባት ማናዬ። ሕዳሴ ግድብ የሺህ ዘመናት የተዛነፈ ታሪክን መልስ የሰጠ ነውም ብሏል። ጥንተ ጠላቷ ግብጽ ግን አሁንም የኢትዮጵያን ጉስቁልና እንጅ ለውጥ ማየት ያሰክራታል ብለዋል።

ለዚህም ከሰሞኑ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላይ እና በሌሎች መድረኮች የምታደረጋቸው ተገቢ ያልኾኑ ክሶች ማሳያ ሊኾን እንደሚችሉም አንስቷል። ያም ኾኖ ይላል ስለአባት የግብፅ የዓባይ ውኃ ሙግት በዓለም አደባባይ የረፈደበት እንደኾነ ገልጿል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከሕዳሴ አልፋ ትልልቅ ቀልብ ሳቢ ፕሮጀክቶችን ጀምራለች ነው ያለው። የግብፅ የተንኮል ልብ አርፎ ባይተኛም ኢትዮጵያውያን ግን ዛሬም እንደትናንቱ ታሪክ መፈጸም እንችላለን ብሏል።

ከፍትሕ ባፈነገጠ አኳዃን ከይዞታዋ የወጣውን የባሕር በር ጉዳይም እንደ አብነት አንስቷል።

ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ አሁን ላይ ትልቁ አጀንዳዋ መኾን አለበት ባይ ነው። ይህ ሲኾን ግን ግብፅ እና መሰሎቿ አርፈው ይተኛሉ ማለት አይደለም ነው ያለው። ምክንያቱም እነዚህ ትልልቅ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያ የለውጥ ምሥጢሮች ናቸውና ብሏል።

ከስዊዝ ካናል መከፈት ጀምሮ የምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ዘዋሪ ኾና ለቆየችው ግብፅ እንዲህ አይነት ፍትሐዊ ጥያቄዎች አይመቿትም እና በየመድረኩ ክሷን አጠናክራ ለመቀጠሏ የባሕር በር ጥያቄም ስጋቷ እንደኾነ ነው የገለጸው።

ምንም ይሁን ምን ግን ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ፍትሐዊ ይዞታዋ ነው ብሏል። ኢትዮጵያ በታሪኳ ካልነኳት የማትነካ፤ ከተናጠላዊ አካሄድ ይልቅ የጋራ ደኅንነት ላይ የምታተኩር ሀገር እንደኾነችም ገልጿል። በታሪክም የሊግ ኦፍ ኔሽን እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ኅብረቶች መሥራች መኾኗን አንስቷል።

የፓን አፍሪካኒዝምን ችቦ ለኩሳ ለብዙ ሀገራት ነጻነት አርዓያ የኾነችን ሀገር በሀሰት በየመድረኩ መወንጀልም ኢትዮጵያን ገላጭ አይደለም ባይ ነው። የባሕር በር ጥያቄን እውን ለማድረግ ሕዳሴ ግድብ ላይ ያሳየነውን ዲፕሎማሲ እንደ እርሾ መጠቀም ይኖርብናል ነው ያለው።

“ቀይ ባሕርን በተመለከተ የታሪክ እዳው ከኋላችን ቢኾንም ትልቁ የታሪክ አደራችን ያለው ግን ከፊታችን ነው” ብሏል። ከዚህ በፊት አንዳንድ ጻሕፍት ኢትዮጵያ ከባሕር ወጥታ ጤዛ ትልሳለች ብለው ሲጽፉ ተስተውለዋል፤ ከዚህ በኋላ የታሪክ ተወቃሽነት በዚህ ትውልድ ማብቃት አለበት ብሏል።

ኢትዮጵያ ለምሥራቅ አፍሪካ ደኅንነት መልህቅ ናት የሚለው ስለአባት ይህ በቀጣይ እንዲጠናከር ግን ቀይ ባሕር ወደ ይዞታው መመለስ አለበት ነው ያለው።

የተያዘው ትልቅ አጀንዳ እውን እንዲኾን ታዲያ ዲፕሎማሲን ማላቅ እና የውስጥ አንድነትን ማጠንከር መሠረታዊ ነጥቦች እንደኾኑ ጠቁሟል።

ዘጋቢ:- ሰለሞን አንዳርጌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
        👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሀገራት ለምን ቲክቶክን ያግዳሉ?
Next articleየጎንደር መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ግንባታ ከ72 በመቶ በላይ ደርሷል።