
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮች መስፋፋት እየጨመረ ሲመጣ የቲክቶክ ተጽዕኖ እና የተጠቃሚዎቹ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ አድጓል።
ይሁን እንጂ ቲክቶክ በተለያዩ ሀገራት ዘንድ የብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት መፍጠሩን በዚህ ጽሑፍ ለመረጃነት የተጠቀምንባቸው ድረ ገጾች ያመላክታሉ።
በዚህ ምክንያት በዓለማችን 20 የሚደርሱ ሀገራት በተለያየ ደረጃ በቲክቶክ ላይ እገዳ ጥለዋል።
እነዚህ እገዳዎች ሙሉ በሙሉ በሀገር ግዛት ውስጥ እንዳይሠራ መከልከል፣ በብሔራዊ ተቋማት እና በመንግሥት ባለቤትነት ሥር ባሉ ኮምፒውተሮች እና ስልኮች እንዳይሠራ ማገድ፣ የመንግሥት ሠራተኞች እንዳይጠቀሙ መከልከል፣ በኦንላይን ግብይት ላይ እገዳ መጣል እንዲሁም በሕዝብ አገልግሎት መስጫ መገልገያዎች ላይ የሚጣሉ ገደቦችን ያካትታሉ።
እርምጃ ከወሰዱት ሀገራት መካከል አሜሪካ፣ ብሪታንያ፣ ታይዋን፣ ካናዳ፣ ሕንድ፣ አውስትራሊያ እና ሶማሊያ ይገኙበታል። በጣም የሚገርመው ደግሞ የቲክቶክ ባለቤት በኾነችው ቻይናም ሙሉ በሙሉ እንዳይሠራ መታገዱን ኢንዲያን ኤክስፕረስ ዘግቧል።
ተንደር ቢት የተሰኘው ድረ ገጽም በ2025 የቲክቶክ ተጠቃሚዎችን የተመለከተ መረጃ ይዞ ወጥቷል። ይህ የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጭ በአሁኑ ወቅት 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን የሚጠጋ ቋሚ ወይም ንቁ ተጠቃሚዎች አሉት።
በተጨማሪም በየቀኑ 34 ሚሊዮን ቪዲዮዎች እንደሚጫኑበት እና እያንዳንዱ ሰው በየቀኑ በአማካይ 58 ደቂቃ በቲክቶክ ላይ እንደሚያጠፋ መረጃው ያመለክታል።
ሀገራት ቲክቶክን ለመከልከል ከሚያነሷቸው ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ የመረጃ እና ብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት፣ የሚለቀቁ ይዘቶችን ለሌላ ዓላማ የመጠቀም አጋጣሚ እንዲሁም ሀገራዊ ባሕል እና እሴቶችን ጠብቆ ለማቆየት የሚሉ ጉዳዮች ይገኙበታል።
ከሌሎች ለየት ባለ መልኩ አልባኒያ በ2024 መጨረሻ ላይ እገዳ ለመጣል ምክንያት ያደረገችው በሀገሪቱ የሚከሰተውን ጥቃት እና ትንኮሳ ከፍ በማድረግ በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ አለው በሚል ነው።
ቲክቶክን የፈጠረውን ባይት ዳንስ የሚባለውን የቻይና ኩባንያን የመሠረተው ዛንግ ይሚንግ እንደሚባል እና የቀድሞ የማይክሮሶፍት ሠራተኛ እንደነበር ሲኤንኤን በመጋቢት ወር 2023 ዘግቧል።
ይህ ኩባንያ መጀመሪያ የፈጠረው ማኅበራዊ ሚዲያ መተግበሪያ ዶይን (Douyin) ይባላል። በ2016 ነው አገልግሎቱን የጀመረው። በመንግሥት ሙሉ ቁጥጥር የሚደረግበት እና አሁንም በቻይና ውስጥ አገልግሎት ላይ ይውላል። ከዓመት በኋላ ደግሞ ራሱ ባይት ዳንስ ቲክቶክን ይፋ አድርጓል። ምንም እንኳ በቻይና ግዛት እገዳ ቢጣልበትም፡፡
ቻይና ቲክቶክን በግዛቷ የከለከለችበት ዋና ዋና ምክንያቶች የኢንተርኔት መረጃ ፍሰትን ለመቆጣጠር፣ የኮሙኒስት ቻይና ፓርቲን እሴት ለመጠበቅ፣ በመንግሥት ቁጥጥር በሚደረግበት ዶይን እና በታገደው ቲክቶክ መካከል የተለያየ የአጠቃቀም ሕግ ለመተግበር፣ ለታዳጊዎች አርዓያ መኾን የሚችሉ ይዘቶች በመንግሥት እንዲረጋገጡ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚኖርን ቆይታ ለመገደብ እና የቻይናን ብሔራዊ ትርክት ለማጎልበት ሲባል ነው።
ሀገራት ከብሔራዊ ደኅንነት፣ ከመረጃ እና ከእሴት ጥበቃ አንፃር የራሳቸውን ምክንያቶች ቢያስቀምጡም ብዙ ሰዓታትን እንደ ቲክቶክ ባሉ የማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ማሳለፍ በጤናው ዘርፍም ጉዳቶች እንዳሉት የአሜሪካ የሥነ ልቦና ጆርናል ላይ የወጣ ጽሑፍ ይጠቁማል።
ይህንን ጽሑፍ ዋቢ በማድረግ ኤንቢሲ ኒውስ (NBC News) ድረ ገጽ እንደዘገበው ከኾነ ብዙ ቪዲዮዎችን መመልከት የድባቴ፣ የፍርሃት፣ የጭንቀት እና የብቸኝነት ስሜትን ከፍ ያደርጋል።
በተጨማሪም ረጅም ጊዜን ቪዲዮዎችን በመመልከት ማሳለፍ ትኩረት ማጣትን እና የትምህርት አቅምን እንደሚያዳክም ጠቅሷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
