የግብፅ መሪዎች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለሥልጣን ማራዘሚያነት እየተጠቀሙበት ነው።

49

አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ፕሮፌሰር አደም ከሚል በአረብ ሀገራት እና በኢትዮጵያ መካከል ስላለ ግንኙነት በርካታ ጥናቶችን ሠርተዋል። ከአሚኮ “የእኛ ጉዳይ” ዝግጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ በአረብኛ ቋንቋ ዛሬም ኢትዮጵያን የረሃብ ምሳሌ እና የቀጣናው ጠላት አድርገው መልዕክት እያስተላለፉ ይገኛሉ ብለዋል።

አስገራሚው ነገር ግን ኢትዮጵያን ከዓባይ የራቀች ሀገር አድርገው ግብፆች የሚስሉበት መንገድ 86 በመቶ የውኃ ባለቤቷ የኾነችው ኢትዮጵያ የመጠቀም መብት እንደሌላት ዛሬም ይሰብካሉ።

በሌላ በኩል አንዲት ግብፃዊት እናት ልጇን ስታጠባ ይህ በዓባይ ውኃ ምክንያት የተገኘ እንጂ የግሌ የጡት ወተት አይደለም በሚል ትመግበዋለች ይላሉ። ይህ የሚደረገው ከፍ ያለ ትስስር ከዓባይ ጋር እንዲኖረው ለማድረግ ነው።

አንድ ግብፃዊ ወታደር ቃለ መሐላ ሲፈፅም ለሀገሬ እሞታለሁ፤ ለዳር ደንበሯ እሰዋለሁ ብሎ አይደለም ለሕዝቤ ዋጋ እከፍላለሁ ብሎም አይደለም ለዓባይ እሞታለሁ ብሎ እንጂ።

ግብፅ የኢትዮጵያ ጉዳይ ስታቦካ ስትጋገር የምትውለው ከጥንት ጀምሮ በአረብኛ ቋንቋ ቢኾንም ኢትዮጵያ ይህንን ትኩረት አላደረጋችበትም፤ የሚዲያም የውጭ ግንኙነት አቅጣጫዋን በሚገባው ልክ አልሠራችም ብለዋል።

ግብፃውያን በአንፃሩ ከዲያስፖራ እስከ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ሚዲያዎች ትኩረት አድርገው የሚሠሩ በመኾኑ ሊተኮርበት ይገባዋል ይላሉ።

10 ሚሊዮን ግብፃውያን ዲያስፖራዎች በተለያዩ ዓለማት ይገኛሉ። ሐኪሞች ብቻ 150 ሺህ ናቸው፤ በየዘርፉ በዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ገብተው የሚሠሩ በርካታ ናቸው። በቢቢሲ አረብኛ፣ ቪኦኤ አረብኛ፣ በዶቸቬሌ አረቢክ፣ በአልጀዚራ አረቢክ፣ በሞንቴካርሎ እና በሌሎችም አረብኛ በሚነገርባቸው ሚዲያዎች ውስጥ ግብፃውያን በመምራት ጭምር አሉ።

ኢትዮጵያ ግን ታሪኳ፣ ሥልጣኔዋ፣ እድገቷ እና ሕዝባዊ ትስስሯ ከአረብኛ ቋንቋ ከሚጠቀሙ ሀገራት ጋር ኾኖ ሳለ መጠቀም ጋር ግን እጅግ ዝቅተኛ ነው ይላሉ። ይህ ደግሞ በሚዲያ አጠቃቀምም ኾነ በውጭ ግንኙነት ዘርፍ የሚታይ መኾኑን አስረድተዋል።

ዓባይን መሠረት አድርገው በ1875/76 ዓ.ም ግብፃውያን ኢትዮጵያ ላይ የቀጥታ ጦርነት ከፈቱ፤ ኢትዮጵያውያን በሚገባ መከቱ። ቀጥሎ የጀማል አብዱል ናስር ዘመን ነበር።

በዚህም ግብፅ ከጦርነት ይለቅ ኢኮኖሚ ላይ በማተኮር የአስዋን ግድብ ገነባች። በአንዋር ሳዳት ዘመን ደግሞ በቀጥታ በተላለፈ ዝግጅት ኢትዮጵያ ዓባይን እገድባለሁ ካለች አጠፋታለሁ አሉ። ያንን ጊዜ ፕሮፌሰር አደም በቴሌቪዥን ይከታተሉ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ከዚያም የመጣው የሁስኒ ሙባረክ ዘመን ደግሞ ሱዳን አካባቢ የጦር ሰፈር መስርቶ የኢትዮጵያን በዓባይ ወንዝ ግድብ የመሥራት ፍላጎትን ለማሰናከል ሞከረ፤ ይሁንና ፍላጎቱ ሳይሳካ ቀረ።

የሙሀመድ ሙርሲ ዘመን መጥቶ ኢትዮጵያ ላይ ጦር ማዝመት እቅዳቸውን በቀጥታ ቴሌቪዥን አስተላለፉ፤ አሁንም አልተሳካም። ይልቁኑ ግን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መሠረት ተጣለ። ቀጥሎም ከአልሲሲ ዘመን መንግሥት ጋር እየታገለች ኢትዮጵያ ግድቧን መገንባት ቀጠለች።

በአልሲሲ ዘመንም እጅግ ዘመናዊ ፈረንሳይ ሠራሹ ሚሳኤል ጣይ “ራፋል” የተባለ የጦር ጀት ግብፅ ሕዳሴ ግድብን በደረቁ ለመምታት ብቻ በሚል ገዝታ ነበር። ይሁንና ከተባለው ጊዜ በፊት ውኃ መያዝ በመቻሉ ይህ እቅድ መክሸፉን ያስታውሳሉ። በተከታታይ ውኃ ተሞላ ሕዳሴም ተጠናቀቀ። አሁን ራሱን ከሚጠብቅበት እና ከማይደፈርበትም ደረጃ ላይ ደረሰ።

በ2012 ዓም ዓባይ ችግር ውስጥ ወድቋል በሚል 34 ቢሊዮን ዶላር ከዲያስፖራው የሰበሰበው የአልሲሲ መንግሥት አሁንም ችግር ውስጥ ነኝ ማለቱን ቀጥሏል ይላሉ።

ይህን የሚያደርጉት ዋናው ምክንያት ደግሞ ለሥልጣን ማራዘሚያነት ለመጠቀም በማቀድ ነው፤ ሌላም የገቢ ምንጭ የማድረግ ፍላጎት መኾኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያን የማዳከም ሴራ የማጀት አጀንዳ አድርገው እየናወዙበት ነው። ኢትዮጵያ ሰላም አይደለችም በሚልም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ኢትዮጵያ ላይ እንዳይሠራ፣ ከተሠራም አደጋ እንዳለበት እየገለጹ ይገኛሉ። ሀገር እና ሕዝብ ይህንን የግብጽ የረዘመ ዘመን ተቃርኖ እና ሴራ አጢነው ይሥሩ የፕሮፌሰር አደም ከሚል መልዕክት ነው።

ዘጋቢ:- አንዱዓለም መናን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዓይናችሁን ከዓላማችሁ ላይ አትንቀሉ” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next articleየአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከኮምቦልቻ ከተማ ወጣቶች ጋር እየተወያዩ ነው።