“የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያድግ ከተፈለገ ተቋማትን በቴክኖሎጂ ማዘመን ይገባል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

36

አዲስ አበባ: ኅዳር 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሁለተኛው የኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ ጉባዔ በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ ጀምሯል። በጉባዔው ብሔራዊ የዲጂታል ክፍያዎች ስትራቴጂ (NDPS 2026–2030) እና ፈጣን የክፍያ ሥርዓት (instant payment system IPS) ይፋ ተደርጓል።

ስራቴጂው የእርስ በርስ መስተጋብርን ለማጠናከር ፣ እምነትን ለማሳደግ እና በኢትዮጵያ ዲጂታል የፋይናንስ ሥነ ምህዳር ውስጥ ፈጠራን ለማበረታታት የሚያስችል የአምስት ዓመት ፍኖተ ካርታ እንደኾነ በዕለቱ ተገልጿል።

በጉባዔው መክፈቻ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ግብን ማሳካት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ወሳኝ ነው ብለዋል።

በዲጂታል ፋይናንስ መሠረተ ልማት ተግባራት ብዙ አገልግሎቶች ወደ ዲጂታል ሥርዓቶች መግባታቸውን እና የ5 ሚሊዮን ኮደርስ፣ የብሔራዊ መታወቂያ እና የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን በምሳሌነት አንስተዋል።

“የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያድግ ከተፈለገ በአዲሱ የብሔራዊ ዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂ በርካታ ዜጎችን ተደራሽ ማድረግ እና ተቋማትን በቴክኖሎጂ ማዘመን ይገባል” ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ለዚህም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለስኬቱ እንሠራለን ብለዋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ.ር) የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለማሳደግ ከተወሰዱ እርምጃዎች አንዱ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ነው ብለዋል። በዚህም ቴክኖሎጂን ለማሳደግ፣ የዲጂታል መሠረተ ልማትን ለማሟላት እና ዲጂታል የፋይናንስ ሥርዓትን ለማጠናከር በተሠራው ሥራ አሁን ላይ የዲጂታል ክፍያ በእጥፍ ማደጉን ገልጸዋል።

በተለይ የባንክ ሥርዓቱ የነበሩበትን የቴክኖሎጂ ችግሮች ለመቅረፍ በክፍያ ሥርዓት ላይ ዲጂታል አሠራር መዘርጋቱን አንስተዋል። በፈጠራ የዳበሩ ተቋማትን ለመፍጠር አሁንም ብዙ ሥራዎች እንደሚቀሩ ያነሱት ዶ.ር እዮብ በተለይ በዲጂታል ክፍያ ላይ የሚታዩ የዳታ በገጠር እና በከተማ ያለው የተደራሽነት ልዩነት፣ የመረጃ ደኅንነት እና ውስን መረጃ መኖር፣ የዲጂታል መሠረተ ልማቶች ላይ ያሉ ክፍተቶችን መሙላት ይገባል ብለዋል።

የአፍሪካ አሕጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ዋና ጸሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ በበኩላቸው የ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ሕዝብ ባለቤት የኾነችው አፍሪካን የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ማሳደግ የአሕጉሪቱን የንግድ ልውውጥ ለማሻሻል ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በዘርፉ የጀመረችው ጥረት ለአሕጉሪቱ ወሳኝ መኾኑን ጠቅሰው ያለ ዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ኢኮኖሚን ማሳደግ፣ ኢንዱስትሪን ማጠናከር እና የሥራ ፈጠራን ማሳደግ አይታሰብም ብለዋል።

በቀጣይ ጥቂት ዓመታት የምንሠራቸው ሥራዎች አንድ ወጥ አሕጉራዊ መገበያያ የኾነው የፓን አፍሪካ ክፍያ ሥርዓትን እውን ማድረግን ጨምሮ የሀገራቱን ኢኮኖሚ በፍጥነት ለማሳደግ ቁልፍ መኾኑን ነው የገለጹት።

እስከ ነገ የሚቀጥለው ሁለተኛው የኢትዮጵያ ዲጂታል ክፍያ ጉባዔ ከፋይናንስ ዘርፉ ከ300 በላይ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላትን ባሰባሰበው የመጀመሪያ ኮንፈረንስ ስኬት ላይ የተመሠረተ ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ለፋይዳ መታወቂያ ደኅንነት የሚውል የዲጂታል ሠርተፍኬትን በይፋ አስጀመረ።
Next articleየመታመን ዋጋው ከ8 ነጥብ 4 ሚልየን ብር በላይ ሲሆን!