የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ለፋይዳ መታወቂያ ደኅንነት የሚውል የዲጂታል ሠርተፍኬትን በይፋ አስጀመረ።

15

አዲስ አበባ: ኅዳር 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከጥቂት ወራት በፊት ለኢ-ፓስፖርት አገልግሎት ዲጂታል ሠርተፍኬት ለማምረት የሚውለውን የሩት ሠርተፍኬት ባለሥልጣን ያስጀመረው አሥተዳደሩ በዛሬው እለትም በተመሳሳይ ለፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ደኅንነት የሚውለውን አገልግሎት በይፋ አስጀምሯል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትግስት ሀሚድ የአገልግሎቱ አላማ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓትን አስተማማኝ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ከጥቃት የተጠበቀ መኾኑን ለማረጋገጥ የሚውል ዲጂታል ሰርተፍኬቶችን ማምረት የሚችል የሩት ሠርተፍኬት ባለሥልጣን በይፋ ማስጀመር ነው ብለዋል።

ከዛሬ ጀምሮ የፋይዳ መታወቂያን ለመውሰድ የሚመዘገቡ ዜጎች በዲጂታል ሠርተፍኬት አገልግሎትን የሚያገኙ መኾኑንም ዋና ዳይሬክተሯ አክለዋል። የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ሥራ አስኪያጅ ዮዳሄ አርዓያ ሥላሴ በበኩላቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ29 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ፋይዳ መታወቂያን ለማግኘት ቢመዘገቡም በፍላጎት አሳትሞ የወሰደው ሰው ግን ከ7 ሚሊዮን አይበልጥም ብለዋል።

ከዚህ ቀደም አገልግሎት ላይ ሲውል የነበረው ፋይዳ መታወቂያ ቁልፍ መሰረተ ልማት ጋር ያልተሳሰረ እንደነበር በመግለፅም በዛሬው እለት የሚካሄደው የዲጂታል ፊርማ ሥነ ሥርዓትም ሠርተፍኬቱ ፋይዳን ከብሔራዊ ቁልፍ ዲጂታል ሠርተፍኬት ጋር የሚያናብብ ነው ብለዋል።

የይፋዊ ቁልፍ መሰረተ ልማት ኦፕሬሽን ክፍል ኀላፊ ዳንኤል ታደሰ ከዚህ በኋላ ለፋይዳ መታወቂያ የሚያመለክቱ ዜጎች የደኅንነት ማስጠበቂያ ቁልፍ መሰረተ ልማት የተሟላለትን መታወቂያ በካርድ ማሳተም ሳይጠበቅባቸው በቀላሉ ሚስጥራዊ ኪውአርኮዱን ስካን በማድረግ ለተለያዩ አገልግሎቶች መጠቀም የሚችሉት መኾኑንገልጸዋል።

በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ያጋጥም የነበረውን የማንነት ሥርቆትን በመከላከል በቀላሉ ተመሳስሎ መታተምን ሙሉ በሙሉ የሚከላከል መኾኑን ጠቁመዋል።

ነባሩ ፋይዳ መታወቂያም የራሱ የኾነ የደኅንነት ማረጋገጫዎች እንደተጠበቁ ኾነው ጥቅም ላይ መዋሉ ይቀጥላል የተባለ ሲኾን ወደ አዲሱ ሥርዓት መግባት ለሚፈልጉ ዜጎችም አገልግሎቱ ክፍት ነው ተብሏል።

ዘጋቢ:- ቤተልሄም ሰለሞን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየሰባተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ የድምፅ መስጫ ቀን ግንቦት 24/2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ ይፋ ኾነ።
Next article“የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያድግ ከተፈለገ ተቋማትን በቴክኖሎጂ ማዘመን ይገባል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ