
አዲስ አበባ: ኅዳር 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛውን ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በተመለከተ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል። ቦርዱ ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን የተናገሩት የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላት ወርቅ ኃይሉ ናቸው።
ሊካሄድ ስድስት ወራት ብቻ የቀሩት ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫን በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ለማድረግ ቦርዱ ቅርንጫፍ ጣቢያዎችን እና የምርጫ ጽሕፈት ቤቶችን የማደራጀት ተግባር መሠራቱንም ተናግረዋል።
የምርጫ ጣቢያዎች ለሴቶች እና ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲኾኑ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን የተናገሩት ሜላት ወርቅ ኃይሉ የምርጫ እቃዎችን ለማጓጓዝ የመንገዶችን ደኅንነት የማጥራት እና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋርም በተመረጡ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይቶችን ማድረግ እንደተቻለ አመላክተዋል።
በሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የእጩዎች እና የመራጮች ምዝገባ በዲጂታል ሥረዓትም እንደሚካሄድ የቦርድ ሰብሳቢዋ ገልጸዋል። ምዝገባው ከዲጂታል ሥረዓቱ ባለፈ የማንዋል ምዝገባ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
የምዝገባ ሥረዓቱ ራስን በራስ በዲጂታል አማራጭ መመዝገብ እና በምርጫ ጣቢያ ተገኝቶ በምርጫ አስፈጻሚዎች በዲጂታል ሥረዓት እንደሚካሄድ የገለጹት ዋና ሰብሳቢዋ የምርጫው ዕለት የድምፅ መስጠት ክዋኔው ግን በወረቀት ብቻ እንደሚፈፀም ነው ያብራሩት። ሥራውም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር እየተሠራ እንዳለ ተናግረዋል።
ለሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ የፓርቲዎች፣ የግል እጩዎች እና የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም መመሪያ መዘጋጀቱን ነው የገለጹት። ለተወዳዳሪ ፓርቲዎችም ኾነ እጩዎች የሚሰጠው የገንዘብ ጉዳይም በተሻሻሉ መመሪያዎች መሠረት እንደሚፈጸም ተናግረዋል።
በሀገሪቱ 22 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች እና 709 የምርጫ ክልሎች ያሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ ለማጠናቀቅ ከክልል መንግሥታት እና ከጸጥታ አካላት ጋር በመነጋገር የየዕለት የሰላም መረጃን በመቀያየር እና አስቻይ ሁኔታዎችን በማረጋገጥ ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ ለማሥፈጸም በቁርጠኝነት እየተሠራ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የእጩዎችን ምዝገባ ከጥር አንድ እስከ የካቲት 1/2018 ዓ.ም ድረስ መኾኑን ጠቁመዋል። የመራጮች በቴክኖሎጂ ራስን በራስ የመመዝገቢያ ጊዜ ደግሞ ከጥር አንድ እስከ መጋቢት 07/ 2018 ዓ.ም ድረስ የሚያካሂድ ይኾናል ነው ያሉት።
አጠቃላይ የመራጮች ምዝገባ ደግሞ ከየካቲት 07 እስከ መጋቢት 07/2018 ዓ.ም ድረስ ማንዋልን ጨምሮ የሚካሄድ ሲኾን ጠቅላላ የሀገራዊ ምርጫው የድምፅ መስጫ ቀን ደግሞ ግንቦት 24/2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ ይፋ ተደርጓል።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
