
ባሕር ዳር: ኅዳር 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገራችን ኢትዮያጵያ የመሬት ባለቤትነት እና ይዞታ በሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ የሚመራ መሠረታዊ ሃብት ነው፡፡
በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 40(3) የመሬት ባለቤትነት መብት የመንግሥት እና የሕዝብ ብቻ እንደኾነ ተደንግጓል፡፡ ይህ ማለት በግለሰብ ደረጃ መሬትን የመጠቀም እንጂ በባለቤትነት የመያዝ መብት የለም ማለት ነው፡፡
መንግሥት ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ኾኖ ሲያገኘው መሬትን በመጠቀም የተገኘን የግል ንብረት መውሰድ እንደሚችል በዚሁ ድንጋጌ በንዑስ አንቀጽ 8 ስር ተቀምጧል፡፡ መሬቱ ለልማት ሲፈለግ እና በመንግሥት ሲወሰድ ግን አስፈላጊው ካሳ እና የማቋቋሚያ እርምጃዎች ተወስደው መኾን እንደሚገባው ሕግ እና ሥርዓት ተዘጋጅቶለታል፡፡
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሕግ ባለሙያው ደመቀ ይብሬ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበት እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን አሠራር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1161/2011 እና ተሻሽሎ በወጣው አዋጅ ቁጥር 1336/2016 የሕግ ድንጋጌ የተቀመጠለት መኾኑን ያብራራሉ፡፡
አቶ ደመቀ እንደገለጹት የመሬት ይዞታ ማስለቀቅ ማለት በግለሰቦች ወይም በደርጅቶች የተያዙ መሬቶች ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ኾነው ሲገኙ በቋሚነት ወይም በጊዚያዊነት በመንግሥት የሚወሰድበት እና ለልማት የሚውልበት ሥርዓት ነው ብለዋል።
ባለይዞታዎች መሬታቸውን ሲለቅቁ ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሊዳረጉ ይችላሉ። በአፈጻጸሙ ላይ የሕዝብን ጥቅም በማረጋገጥ ሂደት የግለሰቦች የንብረት መብት ማክበር እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡
እንደ ሕግ ባለሙያው ማብራሪያ የመሬት ይዞታን ከማስለቀቁ በፊት መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። የሚለቀቀው መሬት ለሕዝብ ጥቅም የሚውል መኾኑን ማረጋገጥ፣ ለካሳ እና ለመልሶ መቋቋሚያ የሚያስፈልገው ወጭ በማን እንደሚሸፈን መለየት እንዲኹም የካሳ እና ምትክ ቦታ ቀድሞ ማዘጋጀት እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
በአዋጅ ቁጥር 1336/2016 ላይ እንደተመለከተው መሬት ለሕዝብ ጥቅም እንዲውል ሲወሰን የመሬት ይዞታቸውን እንዲለቅቁ ለሚደረጉ ባለይዞታዎች የሚከፈለው ካሳ እና የመቋቋሚያ ድጋፍ ወጪ የሚሸፈንበት ሥርዓት ተቀምጧል ነው ያሉት፡፡
👉 የመሬት ይዞታው እንዲለቀቅ የተወሰነው በፌዴራል መንግሥት ለሚከናወን መሠረተ ልማት እና የማኅበራዊ አገልግሎት ማስፋፊያ ከኾነ የልማት ሥራው የሚካሄድበት የክልል አሥተዳደር ለባለይዞታዎች የሚከፈለውን የንብረት ካሳ፣ የልማት ተነሺ ድጋፍ፣ የኢኮኖሚ ጉዳት ካሳ፣ የሥነ ልቦና ጉዳት ካሳ ወጪ የመክፈል ግዴታ አለበት ብለዋል፡፡
👉 ከዚህ ውጪ የሕዝብ ጥቅም ከኾነ መሬቱ እንዲለቀቅ የተወሰነለት አካል የተዘረዘሩትን ካሳዎች እና የመቋቋሚያ ወጪ ለከተማው ወይም ለወረዳው አሥተዳደር ገቢ በማድረግ ለተነሽዎች እንዲደርስ ይደረጋል፡፡ በዚህ መሠረት የካሳ ገንዘቡ ለልማት ተነሺው ካልተከፈለ የከተማ ወይም የወረዳው አሥተዳደር ከመሬቱ አያስለቅቀውም ነው ያሉት፡፡
ቀደም ሲል የካሳ ግመታ ተሠርቶ ያልተከፈላቸው የልማት ተነሺዎች ግን በነባሩ አዋጅ እንደሚስተናገዱ ተደንግጓል ብለዋል፡፡
👉 እንደ ሕግ ባለሙያው ገለጻ ተነሺዎች ከመነሳታቸው በፊት ቢያንስ ከአንድ ዓመት በፊት እንዲያውቁት ማድረግ ያስፈልጋል። አስቸኳይ በሚኾን ጊዜ ቢያንስ ከስድስት ወር በፊት በማወያየት እንዲያውቁት ማድረግ እንደሚገባም በደንብ ቁጥር 472/12 ላይ ተመላክቷል።
👉 የመሬት ይዞታዎች ለተሻለ የሕዝብ ጥቅም ያስፈልጋሉ ተብለው ቢወሰኑም ባለይዞታዎች የማልማት አቅም እና ፍልጎት ካለቸው ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው በአዋጁ አንቀጽ 7 ላይ ተደንግጎ ይገኛል።
ይሁን እንጂ ማንኛውም ባለይዞታ አለማለሁ በማለቱ ብቻ ቅድሚያ የማልማት መብት የሚሰጠው አይኾንም። የአካባቢው ማስተር ፕላን እና ሊሠራ ከታቀደው ልማት አንጻር እንዲሁም የባለይዞታው የማልማት አቅም በጥንቃቄ ተጠንቶ የሚወሰን መኾኑን ጠቁመዋል።
👉 የካሳ አሰላል እና አከፋፈል እንደ ንብረቱ አይነት፣ መጠን እና ባህሪ መሠረት ተደርጎ የሚፈጸም ነው፡፡ የሚለቀቀው መሬት የከተማ ሲኾን ሦስት የካሳ ዓይነቶች ማለትም የንብረት፣ የኢኮኖሚ ጉዳት እና ከማኅበራዊ ትስስር መቋረጥ ጋር ለሚመጡ ሥነ ልቦናዊ ጉዳቶች የሚከፈሉ ካሳዎች ናቸው።
👉 በመሬቱ ላይ ለሚገኘው ንብረት እና በመሬቱ ላይ ላደረገው ቋሚ ማሻሻያ የወቅቱን እና የአካባቢውን የገበያ ዋጋ መሠረት ያደረገ እና ቢያንስ ዝቅተኛውን የቤት መሥሪያ ዋጋ መሠረት በማድረግ ሊኾን ይገባል።
👉 የኢኮኖሚ ጉዳት ካሳ የሚከፈለው ቦታው በመለቀቁ ምክንያት ከአካባቢው የሚኖሩ እና ያልለቀቁ ሰዎች ቦታው በመለቀቁ ምክንያት ከመቀጠር፣ ከመነገድ ወይም ከማከራየት ያገኙ የነበረው ገቢ ሲቀርባቸው የሚከፈል ካሳ ነው።
👉 የሥነ ልቦና ካሳ በአንድ ጊዜ የሚከፈል ከ25 ሺ እስከ 60 ሺ ሊደርስ የሚችል ካሳ እንደሚከፈል በደንቡ አንቀጽ 30 ላይ ተደንግጓል። የሥነ-ልቦና ጉዳት ካሳው ለሚነሱት ብቻ ሳይኾን ጉዳቱ መድረሱ እስከተረጋገጠ ድረስ ላልተነሱት የማኅበረሳብ ክፍሎችም ተግባራዊ እንደሚደረግ ተደንግጓል።
👉 የሚለቀቀው መሬት የገጠር እርሻ መሬት ከኾነ ከተወሰደበት መሬት ተመጣጣኝ ምርት የሚያስገኝ መሬት (ከተገኘ) እና በተጨማሪነትም ከመልቀቁ በፊት በነበሩት 3 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛውን የ1 ዓመት ገቢ በወቅታዊ ዋጋ ተሰልቶ እንዲከፈለው ይደረጋል።
👉 ለእርሻ ቦታ ምትክ መሬት ካልተገኘለት በመሬቱ ላይ ሲያገኝ የነበረውን ከፍተኛውን ዓመታዊ ገቢ በ15 ተባዝቶ መከፈል አለበት። ከመኖሪያው ለሚነሳ የገጠር ነዋሪ ምትክ ቦታ እና የልማት ተነሺ ድጋፍ ይደረግለታል።
👉 የማስለቀቅ ውሳኔው ከተላለፈ በኋላ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕዝቡን ማወያየት እና አስፈላጊ የሚባሉ የሰነድ ማጥራት፣ የመረጃ ማሰባሰብ፣ ካሳ የመክፈል፣ ምትክ ቦታ የማዘጋጀት እንዲኹም መልሶ ስለማቋቋም ሥራዎች መሠራት ይኖርባቸዋል።
ይህንን ሥርዓት በአግባቡ መተግበር በወቅቱ ካሳ ባለመክፈል እና መሬትን ከሦስተኛ ወገን የይዞታ ጥያቄ ነጻ ባለማድረግ ምክንያት የሚከሰቱ የልማት ፕሮጀክቶች መጓተትን ያስቀራል፡፡
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
