
ባሕር ዳር: ኅዳር 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የፖሊስ አባላት እና ሲቪል ሠራተኞች በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ለ21ኛ ጊዜ “ትውልድን ለሥነ ምግባር፣ ተቋምን በአሠራር” በሚል መሪ መልዕክት የፀረ ሙስና ቀንን አስመልክቶ ውይይት እያካሄደ ነው።
መድረኩ” አካል ጉዳተኝነትን የሚያካትት ማኅበረሰብ መገንባት ለተሻለ ማኅበራዊ ዕድገት” በሚል መሪ መልዕክት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ33ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአካል ጉዳተኞች ቀንንም ያካተተ ነው። የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀብታሙ ሲሳይ ተቋማችንን ከሙስና እና ከብልሹ አሠራር ነጻ ለማድረግ ከዚህ በፊት በተለያዩ መንገዶች ፍተሻ አድርገናል ብለዋል።
በቀጣይም ተቋሙን ተወዳዳሪ እና ከሙስና የጸዳ ማድረግ ይኖርብናል ነው ያሉት። “ሙስና የሀገርም የተቋማትም እድገት ፀር እንደኾነ ነው የገለጹት። “ሁላችንም የፀረ ሙስና ትግሉ አቀጣጣይ ችቦዎች መኾን ይኖርብናል” ነው ያሉት።
ከዚህ በፊት የነበሩ ብልሹ አሠራሮችን ወደ ሲስተም በማስገባት የፀረ ሙስና ትግልን ልንከተል እና ልንተገብር ይነባልም ብለዋል። አካል ጉዳተኝነት ሰዎች ፈልገውት የሚያመጡት አይደለም፤ ይልቁንም በማንኛውም ሰው ላይ መቸ ሊከሰት እንደሚችል አይታወቅም ነው ያሉት።
ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታ መፍጠርን ለራሳችን ብለን እንዳደረግነው መቁጠር ይኖርብናል ብለዋል ኮሚሽነር ሀብታሙ። አካል ጉዳተኞች ምጡቅ አዕምሮ ያላቸው፤ ለሀገር ብዙ አስተዎጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ ናቸውም ብለዋል።
እንደ ተቋም ምቹ ሁኔታዎች ሊመቻችላቸው እንደሚገባም አንስተዋል።
ዘጋቢ:- ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
