
ባሕር ዳር: ኅዳር 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ቢሮ፣ ከዩኒሴፍ እና ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር ክልላዊ የተቀናጀ የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ስሜነህ አያሌው አማራ ክልልን ከሚያጋጥሙት ችግሮች መካከል አንዱ ፖሊዮ በሽታ መኾኑን ገልጸዋል።
በሽታው ሽባነትን የሚያስከትል እና ለሞት የሚዳርግ መኾኑን አንስተዋል። መከላከል የሚቻለው ለሕጻናት ክትባት በመስጠት መኾኑንም አክለዋል። መደበኛ፣ የዘመቻ ክትባት እንዲሁም የአሰሳ ሥራ እና ክትባት ማድረግም ስልቶች መኾናቸውን ጠቅሰዋል።
በሽታው በዓለም ደረጃ ጠፋ ቢባልም በአማራ እና አጎራባች ክልሎች መልሶ መከሰቱን አንስተዋል። ለዚህም የፖሊዮ መከላከያ ክትባት መሰጠት መጀመሩን ተናግረዋል። በአራተኛው ዙር ዘመቻ ከ5 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ይከተባሉ። ለዚህም ከ39 ሺህ በላይ አባላት ያሉት 13 የከታቢ ቡድን መደራጀቱን ገልጸዋል።
ክትባቱ በቤት ለቤት፣ በመጠለያ ጣቢያ እና በትምህርት ቤቶች ይሰጣል። ለክትባት ዘመቻው መሳካት ትብብር እና ቅንጅት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የዘመቻው አካላትም በየደረጃው ግንዛቤ በመፍጠር እና በማስተባበር እንዲያግዙ ጠይቀዋል።
ወላጆችም ሕጻናትን እንዲያስከትቡ አደራ ብለዋል። የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አበበ ተምትሜ የፖሊዮ የተቀናጀ ክትባት ዘመቻ የሕጻናትን ሕይወት ለመታደግ ዘርፈ ብዙ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።
የክትባት አገልግሎት በመስጠት የምንከላከላቸውን በሽታዎች ለማጥፋት ብዙ ሥራ ይጠይቀናል። ከዚህ ቀደም በተሠራው ሥራ ብዙ ውጤት መገኘቱንም ጠቅሰዋል።
ለሕጻናት 15 ዓይነት ክትባቶች እየተሰጡ መኾኑን ጠቅሰው የፖሊዮ ክትባት ዘመቻም ትብብር ስለሚያስፈልገው የአጋር አካላትን ትብብር እንደሚፈልግ ተናግረዋል።
ክትባቱ ቤት ለቤት እንዲደርስ መረጃ ለማድረስ እና የደኅንነት ጥበቃ በማድረግ የሚዲያ እና የጸጥታ አካላት ዘመቻውን ለማሳካት እንዲተባበሩ አሳስበዋል።
ምክትል ቢሮ ኀላፊው ከታህሳስ 3 እስከ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚደረገው የፖሊዮ መከላከያ ዘመቻ ቅድመ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
