
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 20ኛው የኢትዮጵያ የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል “ዴሞክራሲያዊ መግባባት፣ ለኀብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልዕክት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ እየተከበረ ይገኛል።
የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር የዘንደሮው በዓል የጋራ ትርክት ውጤት፣ የአንድነት ምልክት እና የቁጭት መገለጫ መኾኑን ተናግረዋል። በዓሉ ዳግማዊ ዓድዋ የኾነው የሕዳሴ ግድብ በተመረቀበት እና የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጅማሮ የተበሰረበት ዋዜማ መከበሩ መኾኑንም አንስተዋል።
ሀገራዊ መዛነፎችን ለማስተካከል ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ ዝግጅት በተጠናቀቀበት እንዲሁም ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫን ለማድረግ መንግሥት በቂ ቅድመ ዝግጅት ባጠናቀቀበት ወቅት በዓሉ መከበሩም አንዱ የበዓሉ ልዩነት ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
አፈ ጉባዔ አገኘሁ የዛሬው በዓል ኢትዮጵያውያን በኀብረ ብሔራዊ አንድነት የደመቀውን ብዝኀ ማንነታችንን ለዓለም የምናሳይበት ነው ብለዋል። በዓሉ ከኩስመና ዘመን በመውጣት ወደ ማንሰራራት፣ ከቁዘማ ወጥተን ወደ መነቃቃት፣ ከጨለማ ወደ ተስፋ ብርሃን የምንሸጋገርበት ብሎም ቃል ኪዳናችንን በጋራ የምናረጋግጥበት ነው ብለዋል።
በመከባበር፣ በመተባበር፣ በእኩልነት እና በአንድነት በጋራ የመልማት ቃል ኪዳናችንን የምናድስበት ነው ያሉት አፈ ጉባኤው የጋራ ቤታችን መሠረት እንደጸና ለማኖር ከጋራ ማንነታችን የተቀዳ ብዝኀነታችንን የሚያጎላ የጋራ ማንነት ሊኖር ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
ይህንን የጋራ ኢትዮጵያዊነት ለማጽናት የሕዝቦችን የዘመናት አብሮነት ለማስፈን የጋራ አሰባሳቢ ትርክት መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል። “እንደ እኛ ብዝኀ ባሕል፣ ሐይማኖት፣ ቋንቋ ባላቸው ሀገሮች ብቸኛው መዳኛ መንገድ ዴሞክራሲያዊ መግባባት ነው” ብለዋል አፈ ጉባዔው።
የለውጡ መንግሥት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማምጣት እና ዘላቂ ሰላም ለማሰፈን አንድነትን የሚያስማማ መንገድ መርጦ እየተንቀሳቀሰ ይገኛልም ነው ያሉት። ይህንም ጅምር እንቅስቃሴ ከከፍታው ለማድረስ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ኀላፊነት ሊኾን ይገባልም ብለዋል። የሀገራችን ሰላም ተጠብቆ እንዲቀጥልም ሁሉም የድርሻውን ማበርከት አለበት ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ወደሚመጥናት ከፍታ ለመውጣት የማንሰራራት ጉዟዋን ቀጥላለች ያሉት አቶ አገኘሁ ጀምራ የማጠናቀቅ አቅሟን ስለማጠናከሯም ገልጸዋል። የማይቻሉ የሚመስሉትን ሁሉ ችላ አሳይታለች፤ ግዙፍ ብሮጀክቶችን ፈጽማለች፤ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ዋና አፈጉባኤው።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
