
አዲስ አበባ: ኅዳር 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገሪቱ እየተመዘገበ የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ እድገት የሀገሪቱን የወደፊት መዳረሻ እና የሕዝቡን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርግ መኾኑን ተሳታፊዎች በዕለቱ አንስተዋል።
ኢኮኖሚያዊ ሪፎርም እና የተመዘገበው የምጣኔ ሃብት እድገት ሀገሪቱን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተቀባይነቷን ያሳደገ መኾኑን ነው ተሳታፊዎቹ የተናገሩት።
ቅርሶችን በመጠበቅ በኩል ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በትብብር መሥራት እንደሚገባም ተነስቷል። ምጣኔ ሃብቱን ለማሳደግ የሚያስችሉ የብድር አቅርቦት እንዲኖርም ተጠይቋል።
ቱሪዝም ከአምስቱ በመንግሥት ትኩረት ከተሰጣቸው መስኮች መካተቱ በዘርፉ ሰፋፊ ኢንቨስትመንት ፈሰስ እንዲደረግ አስችሏል ያሉት ደግሞ የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ ናቸው።
ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ የመስህብ ሃብቶችን በከተማም ኾነ በገጠር በስፋት የማልማት ሥራ እየተከናወነ መኾኑን አስታውቀዋል።
ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በመቀናጀት ቅርሶችን የመጠበቅ፣ የማልማት ሥራ እንደሚሠራም የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ ተናግረዋል።
አራዳ ክፍለ ከተማ ዘመናዊ የከተማ ምስረታ እና እድገት መሠረት የተጣለበት በመኾኑ አካባቢውን በማልማት እና በመጠበቅ የቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በአካባቢው የተገነባው የኮሪደር ልማት ክፍለ ከተማውን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ያግዛል ነው ያሉት።
የፕላን ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር) በተጽዕኖ ውስጥ የቆየውን ኢኮኖሚ እድገት እንዲያሳይ በመንግሥት የተጠና እርምጃ ስለመወሰዱ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ተመስገን ዳረጎት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
