
አዲስ አበባ: ኅዳር 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 20ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ምክንያት በማድረግ ውቧ ሆሳዕና ከተማ የምክክር ቀን መርሐ ግብርን እያካሄደች ትገኛለች።
ሀገራዊ የሲምፖዚየም መድረኩን የከፈቱት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ዕሴቶቻችን፣ ልምዶቻችን እና ባሕሎቻችን እርስ በርስ የምናስተዋውቅበት መኾኑን ተናግረዋል።
ቀኑ ኢትዮጵያ በማንሠራራት ጉዞ ላይ ኾና የሚከበር በመኾኑ ለየት ያደርገዋል ነው ያሉት።
የ2018 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ የሕዝብ ተሳትፎ የተረጋገጠበት፣ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ተዓማኒ ኾኖ “ሥልጣን በምርጫ እና በካርድ ብቻ የሚገኝ መኾኑን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በልዩ ትኩረት መሥራት እንደሚገባቸው” ዋና አፈ ጉባዔው አሳስበዋል።
አዘጋጁ ክልል የሁለት ዓመት ዕድሜ ያለው ቢኾንም ግን ደግሞ የልማት እና መልካም አሥተዳደር ችግሮችን በፍጥነት ምላሽ የሰጠ፤ ጀምሮ መጨረስ እንደሚቻል ያሳየ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያን ታላቅ የማድረግ ትልምን በመያዝ ለሕዝቦች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መሥራት ይገባል ነው ያሉት ዋና አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር።
በሲምፖዚየሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፋጤ ስርሞሎ ቀኑ የኢትዮጵያን እኩልነት እና ብዝኀነት አጉልተን የምናሳይበት ነው ብለዋል።
ቀኑ የአንድነት እና የሀገሪቱ የብልጽግና ጉዞ ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ የምናደርስበት፤ በአብሮነት ኅብረ ብሔራዊ ኾነን የደመቅንብት ልዩ መገለጫ መኾኑንም ገልጸዋል።
በሲምፖዚየሙ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መሥተዳድር እንደሻው ጣሰው (ዶ.ር)፣ የክልል ርእሳነ መሥተዳድሮች፣ የክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔዎች፣ የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ተወካዮች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ:- ኢብራሒም ሙሐመድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
